ዜና ዜና

ጠ/ሚ ዶክተር አብይ በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከተመራው ልዑክ ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ ጋር ተወያዩ።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም የኤርትራ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊና የፕሬዚዳንቱ አማካሪ አቶ የማነ ገብረዓብ ጋርም መወያየታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኤርትራ የልዑካን ቡድን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በአባታቸው ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን የገለጹበትን መልዕክት አድርሰዋል።
በውይይታቸውም የሁለቱን ሀገራት የአንድ ዓመት የሰላም ጉዞ በተመለከተም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት አድርገዋል።

ሁለቱ ወገኖች ባለፈው አንድ ዓመት ግጭትን ለማስወገድ የተደረሰባቸውን ዋና ዋና ውጤቶች በማንሣት በቀጣይ ግንኙነቱን ለማጠናከር መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎችም ተነጋግረዋል።

ኦስማን ሳሌህና የማነ ገብረዓብ ከሃያ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተገኘውን የኤርትራ የልዑካን ቡድን በመምራት በሀገራቱ መካከል የተካሄደውን ወሳኝ የሰላም ድርድር መምራታቸው ይታወሳል።
በሃገራቱ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ለመዘከርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ከሁለቱ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን የዛፍ ችግኝ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተክለዋል።

Average (0 Votes)


No comments yet. Be the first.