ውይይትና መደማመጥን በማጠናከር ሰላማችን እንጠብቅ!

(በክሩቤል)

የረጅም ዘመን የስልጣኔና ተምሳሌት የሆነችው ሀገራችን ዓለም በሁለት ገጽታዎች ያውቃታል፡፡ አንደኛው በምድራችን ውስጥ ከነበሩ ገናና እና አስደናቂ ስልጣኔዎች መካከል የአንዱ ባለቤት መሆንዋ ነው፡፡ የእነዚህን ስልጣኔዎች ማሳያ የሆኑ ሐውልቶች፣ ቅርሶች… ወዘተ የዚህ ህያው ማስረጃዎች ናቸው፡፡  አሁንም የዓላማችን የታሪክ ተመራማሪዎች ያሉፉት የስልጣኔ አሻራ ላይ የሚያደርጉት ጥናትና ምርምር እንደቀጠለ መሆኑን ስንመለከት ሐገራችን የነበረችበት የስልጣኔ ደረጃ መገንዘብ የሚያስችል ነው፡፡ ሀገራችን የውጭ ወራሪዎችን በማሳፈር ረገድ የጀግንነትና የአይበገሬነት ተምሳሌት ሆና ዘልቃለች፡፡ በእነዚህ በስልጣኔና የጀግንነት ጉዳዮች ሀገራችን በዓለም ህዝብ ዘንድ መልካም አድናቆት ስም አትርፋለች፡፡

ሀገራችን የአስደናቂ ስልጠኔና የጀግንነት ተምሳሌት የመሆንዋን ያህል በጊዜ ሂደት በችግር እና ኃላቀርነት የምትታወቅበት ወቅት አሳልፋለች፡፡ በተለይም በተለያዩ ወቅቶች ያጋጠሙ የድርቅ አደጋዎች ዜጎች ለከፋ ችግር በማጋለጣቸው ምክንያት ስመ ገናናዋ ሀገር በመጥፎ እንድትነሳ አድርጎ ቆይቷል፡፡ አሁንም እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ የምትገኝ እንጂ ሙሉ በሙሉ አላሰወገደቻቸውም፡፡ 

ኢትዮጵያ መልካም ስምዋንና ዝናዋን ለመጠበቅ በጊዜ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች ለማስወገድ ትግል ማድረግ ከጀመረች ቆይታለች፡፡ ከሁለት አስርት ዓመታት ጀምሮ በኢህአዴግ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት የሁሉም ችግሮች ዋነኛው መንስኤ ድህነት መሆኑን በማመን ፈጣን ልማት ለማስመዝገብ ተረባርቧል፡፡ በዚህም ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊመዘገብ ችሏል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መልካሙን ጉዞ የሚያስተጓጉሉ ችግሮች መከሰት ጀመሩ፡፡ ሁሌም ወደ ውስጥ የማየት ልምድ ያዳበረው ኢህአዴግ ውስጡን ለመመለከት ወደ ጥልቅ ተሃድሶ ገብቷል፡፡ በዚህም ችግሮቹን ለይቶ ወደ መፍታት ገብቷል፡፡

በዚህም በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምህዳርን የሚያሰፉ በርካታ እርምጃዎች ተወስዷል፡፡ በውጭ ሀገራት የነበሩ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብቷል፡፡ እነዚህ መልካም ስራዎች እንዳሉ ሆነው ግን አሁንም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ሁከቶች፣ የደቦ ፍትህ፣ ስርዓት አልበኝነት ወዘተ በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ በዚህ ችግር ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ያሉ አካላትም ጭምር የችግሩ መፍትሄ ከመሆን ይልቅ የሚባብሱ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡

ኢትዮጵያ ልትደርስበት ያሰበችውን ራዕይ ማሳካት ይቻል ዘንድ አንዱ የሌላውን ሀሳብ የማድመጥ፤ በሌላው ላይ የደረሰውን ችግር ልክ በራስ ላይ እንደደረሰ አድርጎ በጋራ መፍትሄ መፈልግ የግድ ይላል፡፡ የአንዱ ቁስል ሌላው ሊሰማው ይገባል፡፡ የሌላ ስኬት ለማስፋት መስራትም ይገባል፡፡ በአንድ ሀገር ግንባታ ሂደት ላይ የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ አንዲት ሀገር ብሄራዊ ክብሯንና አንድነትዋን የምታስቀጥለው ያለፉ ችግሮች እንዳይደጉሙ በማድረግና ወደፊት በማየት ብቻ ነው፡፡

ሀገራችን አሁን አዲሱን የ2011 ዓም ለመቀበል በመዘጋጀት ላይ ትገኛለች፡፡ አዲሱን ዓመት ስንቀበል በአዲስ አስተሳሰብና መንፈስ መሆን ይገባል፡፡ ግጭት፣ ጥላቻና አለመግባባትን ብሎም የህዝቦችን አንድነት ከሚሸረሽሩ ድርጊቶች መቆጠብ የእያንዳንዱዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ የሰላም መደፍረስ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ ከግጭትና አለመረጋጋት ጥቂት የሴራ ተዋንያን ማትረፍ ይችሉ እንደሆነ እንጂ አብዛኛው ዜጋ ተጎጂ ነው፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ጥያቄዎች ሽፋን የሚነሱ ግጭቶች ለማስቆም መስራት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ማንኛውንም ጥያቄ በህጋዊ አግባብ ብቻ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ ሰላማችንን እና አንድነታችን የሚያጠናክሩ፤ የጋራ እሴቶቻችን ለሚያሳድጉ ጉዳዮች ትኩረት እንስጥ፡፡ የትልቅ ሀገር ባለቤት ሆነን ሰላምን የሚያውኩ ትናንሽ አስተሳሰቦች እናስወግድ፡፡ በሀገራችን ሰላምና አንድነት የበኩላችንን ሚና ለመጫወት ቃል እንግባ፡፡