ዜና ዜና

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህምድ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊነት ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ኢትዮጵያ ላይ ያለውንም ተስፋ ያመላከተ መሆኑን ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንቷ ማምሻቸውን በጠቅላይ ሚኒስተሩ የኖቤል የሰላም ሽልማት የእንኳን ደስ አላችሁ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ መግለጫቸው ሀገር ውስጥ ላሉ እና በውጭ ሀገራት ለሚገኙ መላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንኳን ደስ አላችሁ መልክት አስተላፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ የ2019 የኖቤል የሠላም ሽልማትን በማሸነፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡
ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅርን ከማቀንቀን አቋርጠው እንደማያውቁም አንስተዋል፡፡
በሀገር ውስጥ የነበረውን አስፈሪ የፖለቲካ ፍጥጫ በማርገብ፣ በውጭ ሀገር የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር እንዲገቡ በማድረግ፣ ያለፈውን ታሪክ ዕሴቶች አስጠብቀን እንድንጓዝ ማድረጋቸውንም አንስተዋል፡፡
ስህተቶችንም አርመን፣ አዳዲስ ዕሴቶችን በመጨመር የምንሄድበትን አካሄድ በመንደፍ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውንና ሁለት አሥርተ ዓመታት ያስቆጠረውን ውጥረት በሠላም መፍታታቸውንም አስረድተዋል፡፡
በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ትብብርን በማበረታታት፣ በጎረቤት ሀገራት መካከል የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚቻላቸውን ሁሉ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የዛሬው ሽልማት ዋና ትርጉሙ ለታላላቅ የጠቅላይ ሚኒስተሩ ሥራዎች ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና መስጠቱን አስገንዝበዋል፡፡
ከሁሉም መአዘን እያስተጋባ ያለው የደስታ ስሜት ኢትዮጵያዊያን አንገታችንን በኩራት ከፍ እንድናደርግ የሚጋብዘን እና ልንኮራበት የሚገባ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነንና ተባብረን ሰርተን ያልተሳካልን ጊዜ የለም ያሉት ፕሬዚዳንቷ ፉክክራችንን እርስ በርስ ማድረጋችንን ትተን ከዓለም ጋር ካደረግነው ማሸነፍ እንደምንችል ታሪክ በተደጋጋሚ ነግሮናል ነው ያሉት፡፡
አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ነጻ እንዲወጡ አብረን በመታገል እንደተሳካልን በመግለጽ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲመሰረት ኢትዮጵያ የበኩሏን ማድረጓንም አስታውሰዋል፡፡
የምናተርፈው ከመለያየታችን ሳይሆን ከአንድነታችን፣ ከስንፍናችን ሳይሆን ከሥራችን መሆኑን አይተናል ብለዋል፡፡
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ዓለምን የሚያስደንቅ ሥራ ሰርቶ በዓለም መድረክ ላይ መቆም እንደሚቻልም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት አንዱ መሳያ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያን አንድነትና ጥቅም በማስቀደም ከዚህ በላይ ከሰራን ሥልጣኔያችንና ብልጽግናችን ራሱ ይሸልመናል ብለዋል፡፡
ለኢትዮጵያ ታላቅነት ስንል ችግሮቻችንን በውይይት ለመፍታት፣ ባንስማማም እንኳን ላለመስማማት ተስማምተን፣ በትንንሽ ምክንያቶች ሳንደናቀፍ፣ ሀገራችንን ብቻ አስቀድመን በርትተን እንሥራ ሲሉም ነው መልክታቸውን ያስተላለፉት፡፡

 

2

በኢሕአዴግ ሊቀ መንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ የአለም ሰላም የኖቤል ተሸላሚነትን አስመልክቶ የተላከ የደስታ መግለጫ

የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ የአለም የሰላም ኖቤል አሸናፊነት አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሀገራችን በተከተለቸው የለውጥ አቅጣጫ ላይ ያለውን መተማመንና ተስፋ ያረጋገጠ በመሆኑ የኢህአዴግ ምክር ቤት ለዶ/ር አቢይ አህመድ በተለይ እና ለመላው ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት ይወዳል፡፡

ባለፈው አንድ አመት ከመንፈቅ በድርጅታችን ሊቀ መንበር ዶ/ር አቢይ አህመድ ቀጥተኛ አመራር በሀገራችን ዴሞክራሲን ለማስፈን፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ በርካታ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ሀገራችን ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት በሰላም፣ በመተባበርና በጋራ ብልፅግና ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማድረግ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ከግጭት የፀዳ እንዲሆን ሊቀ መንበራችን ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ወደ ሀገር መሪነት ከመጡ ሁለት አመት እንኳን ያልሞላቸው ቢሆኑም ከሀገር አልፎ አለም ያደነቀውንና የደገፈውን ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ በርግጥም በሀገር አቀፍም ይሁን በውጭ በተንቀሳቀሱባቸው ወቅቶች ሁሉ ስለ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት በመናገርና ይህንኑም በተግባር በማሳየት ያበረከቱት አስተዋፆ ለዚህ ልዩ ክብር የሚያበቃቸው ነው፡፡

በለውጡ የተገኙ ስኬቶችን ከማንም በላይና ቀድመን የምንገነዘባቸውና የፍሬዎቹም ተቋዳሽ እኛው ኢትዮጵያውን ብንሆንም አለም አቀፉ ህብረተሰብ ደግሞ ለዚህ ድላችን በዛሬው እለት በአለም ትልቁን የክብር ሽልማት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በማጎናፀፍ እውቅናውን ቸሯል፡፡ ይህ ሽልማት አለም አቀፉ ህብተሰብ ሀገራችን በተከተለችው የለውጥ አቅጣጫ ላይ ከመተማመን ባለፈ እስካሁን ያስመዘግብናቸው ስኬቶች ዘላቂነት እንደሚኖራቸው ተስፋ ማሳደሩን አመልካች ነው፡፡

ይህ ድል መላ ኢትዮጵያውን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለፈፀሟቸው በጎ ስራዎች በሙሉ የተሰጠ እውቅና በመሆኑ ድሉም የሀገራችን ድል ነው፡፡ በሊቀ መንበራችን ለዚሀ ክብር መብቃት ስሟ ከፍ ብሎ የሚጠራው ሀገራችን ስትሆን አንገታቸውን ቀና አድርገው መሄድ የቻሉት ደግሞ መላ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ሀገራችን እንደቀደመው ሁሉ በየመስኩ አንቱታንና ተቀባይነትን ያተረፉ ጀግኖችን ማፍራት የምትችል መሆኗን አሳይቶናል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትራችን እና አጠቃላይ የለውጥ አመራሩ ጥረት ፍሬ በማፍራቱ ያገኘንው ይህ ሽልማት እንደ መሪ ድርጅት በሊቀ መንበራችን ፋና ወጊነት የጀመርነውን ሰላም የማስፈን፣ የዜጎችን መብትና እኩልነት የማረጋገጥ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች የማረጋገጥ ስራችንን አጠናክረን እንድንቀጥል የሞራል ስንቅ የሚሆነን ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድም በመሪነት ዘመናቸው ከእስካሁኑም የላቀ ስኬት በማስመዝገብ የፓርቲያችንን፣ የመላ የሀገራችንን ህዝቦችንና የሀገራችን ኩራት ሆነው እንደሚቀጥሉ የኢህአዴግ ምክር ቤት ያለውን ሙሉ እምነት እየገለፀ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የመሪያችንን አርዓያ ተከትለን በየተሰማራንበት የስራ መስክ ሁሉ የላቀ ስኬት ለማስመዝገብ እንድንረባረብ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

 

Average (0 Votes)


No comments yet. Be the first.