መጣጥፎች መጣጥፎች

Back

ወደ ታላቅነት የሚወስደው ጉዞ

(በአቡ ኬ)

 

በአለም ላይ ህብረት፣ አንድነት፣ ትብብርና የሚሳሰሉት መሰባሰብን የሚያወሱ ቃላቶች ይዘወተራሉ። የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ አንድነት፣ የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች ወይም USA፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውይም UAE ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

እነዚህ አጠራሮች ቃላቶቹ ስለሚያምሩ ብቻ የመጡ አይደሉም፡፡ ለአመታት ተጸንሶ ምጡ በራሱ ተጨማሪ አመታትን ፈጅቶ የተወለዱ ናቸው። ዛሬ ሃያል የምትባለው አገረ አሜሪካ የመሰባሰብ ውጤት ናት። በተጽዕኖ ፈጣሪነቱ የሚጠቀሰው የአውሮፓ አገራት ህብረት የመሰባሰብ ውጤት ነው። የአለምን አገራት በአንድ የሚያሰባስበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም እንዲሁ።

ምክንያቱም ግልጽ ነው አንድነት ወይም መሰባሰብ ሃይል ስለሆነ፡፡ ድር በያብር አንበሳ ያስር እንደሚባለው ለብቻ መስራት  አንድ ሰው በራሱ ጥረት ብቻ ሊያሳካቸው የማይችሉ ከባድ የሚባሉ ነገሮች እንኳ በጋራ ጥረት ድል ይደረጋሉ፤ ይሳካሉ፡፡ ለብቻ የማይደመጡ ጉዳዮች በጋራ ይደመጣሉ፤ ተቀባይነታቸውም ያን ያህል ይጨምራል፡፡ ወደ አህጉራችን አፍሪካ ስንመጣ ጅምር አንድነትን የሚያጠናክሩ ህብረቶች ቢኖሩም ያንን ይህል በቂና ተፅእኖ መፍጠር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ናቸው ለማለት ይቸግራል፡፡

አፍሪካውያን ከመሰረቷቸው የትብብር መድረኮች መካከል የደቡብ አፍሪካ አገራት የልማት ትብብር SADEC፣ የምዕራብ አፍሪካ ECOWAS እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካውን IGAD መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአፍሪካ ህብረት በየጊዜው በሚያደረግው የውይይት መድረክ ላይ ከሚያነሳቸው አበይት አጀንዳዎች መካከል የአህጉራዊ ትስስርን ማጠናከር ይጠቀሳል፡፡ አጀንዳ 6023 ላይ የተቀመጠውን አገራትን የማስተሳሰር ግብም አንዱ አፍሪካውያን እንደ አህጉር ጠንክረው ለመውጣት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚገለፅበት እቅድ ነው፡፡  

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ብ ብዙ ስራ ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅት በመደመር ፍልስፍናቸው ከአገራዊ አንድነት አልፎ ቀጠናዊ አንድነትን የሚያቀነቅን የጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር አብይ አህመድ ራዕይ ይህንኑ እውን ለማድረግ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መካከል ይጠቀሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንደሚታወቀው ወደ ስልጣን ከመምጣቸው ቀዳሚ ስራቸው ካደረጉት ተግባራት መካከል ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ያላትን ለሁለት አስርት አመታት የተቋረጠውን የወንድማማች ህዝቦች ግንኙነት ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ ነበር። ሁለቱ አገራት ማካከል ተዘገተው የነበሩትን ድንበሮች ከፋፍቶ ህዝቡ በየብስም ይሁን በአየር ትራንስፖርት ተጉዞ እንዲገናኝ አድርገዋል።

በዚህ ተግባራቸው ከሁለቱ አገራት ህዝቦች አልፎ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ  አድናቆት ተችረዋቸዋል፤ እውቅንም አግኝተዋል።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ አላማቸው ሁለቱ አገራት መካከል ሰላም አንዲወረድ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የቀጠናው አገራት ተደምረው በጋራ እንዲያድጉ ማድረግም እንደሆነ ሲናገሩ ተደመጠዋል። ተናግረው ብቻም አላቆሙም በኤርትራና ጂቡቲ መካከል የነበረው የድንበር አካባቢ ግጭት አብቅቶ ሰላም እንዲወርድ ማደራደር ጀመሩ።

በሶማሊያና ኤርትራ መካከል የነበረውም ግንኙነት እንዲሁ ተሻሽሎ ወደ መተባበር እንዲሸጋገር ጥረት ማድረግ ጀምሩ፣ በዚህም እሳቸውን ጨምሮ የኤርትራና የሶማሊያ መሪዎች በተገኙበት የሶስትዮሽ ትብብር ማዕቀፍ አስመራ ላይ ተፈረመ።

በዚያም አላቆሙም በትናንትናው እለትም የኬኒያውን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያትን ይዘው አስመራ ላይ ከተሙ፤ በሶስትዮሽ ግንኙነትና ትብብር ዙሪያም ምክክር አደረጉ።

ዛሬም የሀገረ ኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ይዘው ወደ ደቡብ ሱዳን ጁባ  ተጉዘው የሶስትዮሽ ምክክር እንደሚያደረጉ ነው የሚጠበቀው። ታዲያ የነዚህ ሁሉ ጥረቶች ዋናው ግቡ በምስርቅ አፍሪካ ቀጠና አገራት መካከል ትስስር በመፍጠር፤ በትብብር ማደግ የሚችለበትን መንገድ አብሮ ለመምከር፤ ጠንካራ አህጉራዊ ትስስር ለመፍጠር ነው።

ይህንንም አካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መደመር ብለው ይጠሩታል፤ ማለትም ያለቸውን ደማመሮ ወይም አንድ ላይ አድርጎ አንድ ትልቅ አቅም መፍጠር ማለት ነው። ይህ ደግሞ እውን የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ መሰል ትብብሮች ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ከመገንባት ባሻገር ተፅእኖ ፈጣሪ መሆን ችለዋል፡፡ ህዝቦቻቸውም ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን መርዳት የሚችሉበት አቅም  መፍጠር ችለዋል።

የዚህ ሁሉ መሰረት ደግሞ መንግስታትና ህዝቦቻቸውም መደመር የታላቅነት፣ የሃያልነትና የብልጽግና መሰረት መሆኑን ተገንዝበው ተባበረው ለማደግ ልባቸውንክፍት ማደረግ መቻላቸው ነው።

በአህጉራችን ነባራዊ ሁኔታም የቀጠናውን አገራት ከጦርነት፣ ሽኩቻና ከሽብር ነጻ አወጥቶ ዜጎች እንደልባቸው ተዘዋውረው የሚሰሩበት፤ በአንድ አገር ያለው ወደብ ለሁሉም የሚሆንበት፤ በአንድ አገር ያለው ምርት ሁሉም አገር የሚሸጥበትና የሌለውም የሚሸምትበት ግዙፍ ገበያ መፍጠር ላይ መረባረብ ያስፈልጋል። ያኔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተባብሮ ትልቅ የመሆን ራዕይ እውን ይሆናል።

እኛም እንላለን ዛሬውኑ ለበጎ ነገር መተባበር እንጀምር።