መጣጥፎች መጣጥፎች

Back

አንድ ቤት የሚገነቡ….

በአቡ

አንዳንዴ አባቶቻችን በተረትና በምሳሌያዊ አነጋገር ያወረሱን አባባሎች በጣም የልብ አድርስ ናቸው፡፡ አሁን እየሆነ ያለውን ነገር ሳስበው ከነዚህ ተረቶች መካከል ‘'አንድ ቤት የሚገነባ ሳር አይሰራረቅም'' የሚለው በህሊናዬ አቃጫለ፡፡ ሃቅ ነው፡፡ አንዲት ጎጆ ቤት በጋራ እየገነቡ ያሉ ሰዎች እንዴት ብሎ ለጣሪያ ክዳን የሚሆናቸውን ሳር ይሰራረቃሉ፡፡ ባይሆን ተባብረው ቆንጆና ጠንካራ ሳር ካለበት ፈላልገው ያመጣሉ እንጂ፡፡ ይህን እንዳነሳ ምክንያት የሆነኝ በአገራችን የሚስተዋለው የመጓተትና በተለያየ ጎራ የመፈራረጅ አባዜ የተጠናወተው መብዛቱ ነው፡፡ አንዱ የአንዱን ቡድን ወይም ወገን ስም እየጠራ ያወግዛል፣ አንዱ የሌላኛውን አካባቢ ሰው እየጠራ ጠላትህ ነው እያለ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በቀልና ጥላቻን ይሰብካል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ ደግሞ ይህንን መርዝ ለመርጨት የሚጠቀሙበት ሰፊ ምህዳር እየሆነ መጥቷል፡፡

የአንድ አገር ያውም የአንድ እናት ልጆች፤ እጣ ፋንታችን ሁሉ የተሳሰረ መሆኑ ስለምን ተረሳ? አገር እኮ የጋራ ናት፣ ከክልል ክልል ከከተማ ከተማ ያለው አካፋይ ወሰኖችም እኮ ለአስተዳደር አመቺነት ተብለው የተሰመሩ እንጂ የኔ የአንተ አገር የሚንባባልበት ድንበሮች መሆን አልነበረባቸውም፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀደሙት ጊዜያት የተሰሩ ስህተቶች በይቅርታና በምህረት ታልፈው ታሪኮቻችንንም መማሪያ ብቻ አድርገን ለአገራዊ አንድነት በጋራ አዲስ ታሪክ ለመስራት መነሳት እንደሚገባ በመግለፅ ይህንን የሚያጠናክሩ በርካታ ርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በዚህ የለውጥ ሂደትም ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት፣ የህዝቦቿ አንድነት የተጠበቀና ፍትሃዊነት የተረጋገጠባት አገር ለመገንባት ራዕይ በመሰነቅ አዲስ መንገድ ጀምረናል፡፡

ባለፉት ወራቶች የሰዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ መከበር አለባቸው ከሚል መነሻ የታሰሩት ተፈተዋል፡፡ በአገራቸው አኩርፈው የራቁትም እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡ መከፋፈላችን፤ መጠላለፋችን እንዲያበቃ የእንደመር ጥሪ በማቅረብ ሁሉም ከምንም ነገር በፊት አገሩን እንዲያስቀድም ጥረት ተደርጓል፡፡ ይህ ደግሞ በርካታ ኢትዮጵያውያንን እፎይ ያስባለ እርምጃ ነው፡፡

በአገራችን የተጀመረው ለውጥ ዓላማ በአንድ ላይ ሆኖ ታላቅ የሆነች አገር መገንባት ነው፡፡ አገራችን ተባብረው እንደሚገነቧት አንድ ጎጆ ናት፡፡ ስለዚህ ይህችን የጋራ ቤታችንን ለመገንባት የጀመርነውን የለውጥ ሂደት አጠናክረን በማስቀጠል በውጤቱ የምንረካበትን ጊዜ ልናፋጥነው ይገባል፡፡