መጣጥፎች መጣጥፎች

Back

ከ‹‹እኔ ብቻ›› ስሜት መሻገር ይገባል!!

                                                                                                                                                                                                                 ዘላለም ሲሳይ

በመደመር እሳቤ የጀመርነው ሁሉን አቀፍ አገራዊ ለውጥ እንደ ንብ ታታሪ ሆኖ በመስራት ለውጡን ዳር ማድረስ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ሀላፊነት ነው፡፡ በእኛነት ስሜት በመደራጀት በአገራችን ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በጋራ በመታገል ዛሬ የደረስንበት ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል፡፡ በተባበረ አንድነታችን ያቀነቀንለት የለውጥ ዝማሬ አልፎ አልፎ አንዳንድ መሰናክሎች እያስተናገደ ይገኛል፡፡

በቁልቁለት መንገድ ለማስገባት ከኋላ የሚገፉ ከፊት የሚስቡ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሯራጡ ሃይሎች እዚም እዚያም ይስተዋላሉ፡፡ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ወደ ኋላ ለመመለስ በርካታ ወጥመዶች እየዘረጉ ይገኛሉ፡፡ በብሄሮች መካከል ያለውን ልዩነት በማጉላት በሕዝቦች መካከል ጭቅጭቅና ንትርክ ለመፍጠር የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ በበርካታ ውጣውረድ ታልፎ የተገኘውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ችግሮችን በሠለጠነ እና በሰከነ መንገድ በመፍታት የዴሞክራሲ ባህላችንንም ማሳደግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

አገራችን በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያሉባት አገር እንደመሆኗ መጠን አንድ ከሚያደርጉን አጀንዳዎች ይልቅ የሚያለያዩንን አጀንዳዎች በመፍጠር እነሱ በከፈቱልን የቁልቁለት መንገድ መጓዝ የለብንም፡፡ ትስስራችንን እና አብሮነታችንን ይበልጥ የሚያጠናክርልን የጋራ ቃልኪዳን ሰነድ የሆነው ሕገ-መንግስት አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካላት የመጣስ ሁኔዎች ይስተዋላሉ፡፡ በጋራ ያጸደቅነውን ሕግ በማክበር የአገራችን የዴሞክራሲ እድገት ይበልጥ እንዲያብብ ማድረግ ይገባል፡፡ ሀሳቦች ሁሉ የሚደመጡበትን ሁኔታ በፈጠርንበት የዴሞክራሲ ሥርዓት የኔ ብቻ ይደመጥ የሚል የሥግብግብነት አካሄዶችም መገታት ይገባቸዋል፡፡ የአክሱንም ሀውልት በልዩ ጥበብ ያቆመ፣ ላሊበላን ከድንጋይ ፈልፍሎ የሰራ፣ ጣሊያንን አደብ ያስገዛ የአንድነትና የአረቆ አሳቢነት የኢትዮጵያዊነት ወኔ ተላብሰን ወደ ፊት በአንድነት ወደ ብልጽግናና ገናናነት የሚወስዱን የከፍታ መንገዶችን መከተል ያስፈልጋል፡፡

በትናንሽ አጀናዳዎች ላይ ተጠምደን ከድህነት መውጫ መንገዳችንን ማስተካከል ሲገባ ወደ ቁልቁለት የሚያወርደውን መንገድ መገንባት ኋላቀርነት ነው፡፡ ሰፊና በርካታ ያልተጠቀምንበት የተፈጥሮ ሃብት አገር ባለቤት ሆነን ሳለ በእኔ ብቻ ልጠቀም ስሜት ጠበን መገኘት አይገባንም፡፡ የተሻለች አገር ለመፍጠር ከድህነት ጋር በምናደርገው ትንቅንቅ ትግሉን ለማሸነፍ የሚያስችለንን ስንቅ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከእኔ ብቻ ልጠቀም ስሜት ወደ የጋራ እና እኛ እንጠቀም ወደሚል ስሜት መሻገር ይገባናል፡፡