መጣጥፎች መጣጥፎች

Back

አብሮነታችንን ማን አየብን?

                                                                                                                                                                                            በሚራክል እውነቱ

የኖሮዌይ ስደተኞች ካውንስል በጁን 2018 ባወጣው ዓለም አቀፍ የስደተኞች መረጃ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ኢትዮጵያ በአውዳሚ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ካለችው ሶርያ ትይዩ ላይ ተቀምጣለች፡፡በዚህ መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በመያዝ የመጀመሪያውን ደረጃ ስትይዝ ሶርያ ደግሞ በ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የስደተኛ ቁጥር ትከተላለች፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም ያለባት ሀገር እየመሰለች፤ ነገር ግን በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያውን ቁጥር ከመያዝ ባሻገር በዚህ በኩል በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሱ ካሉት ሶርያ፣ ሶማሊያ፣ የመንና ደቡብ ሱዳን ጋር አብሮ ስሟ መጠራቱ ለኢትዮጵያዊ ማንነት የማይመጥን የአብሮነትየመደጋገፍ ባህላችንን የሚያጠለሽና በሁላችንም ዘንድ በእጅጉ ሀዘኔታን የሚፈጥር ነው፡፡

ሁኔታውን አስፈሪ የሚያደርገው ደግሞ አሁን ካለው አፍራሽ አካሄድ አንፃር በቀጣይም ዜጎች በነፃነት መኖር የሚችሉበት ሁኔታ እንደሌላ ፍራቻ ውስጥ መግባታቸውና ሁኔታው ከመሻሻል ይልቅ መፋናቀሉ ተስፋፍቶ መቀጠሉ ነው፡፡ የዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀል ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመክተት የአገርን ህልውና የሚፈትን መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

እንደኛ ባለች ታዳጊ ሀገር ውስጥ የዜጎች መፈናቀል አብሮ የመኖር ታሪክና ባህል የሚያደበዝዝ፣ የኢትዮጵያን አንድነት የተሰናሰለበትን የአብሮነት ባህልና እሴት የሚሸረሽር  የጥፋት ጉዞ ነው፡፡ አንተ ከዚህ ወገን ነህ አንተ ከዛ ወገን በሚል ዘርን ማዕከል ያደረገ ያረጀ አጥፊ አስተሳሰብ ተሸካሚ መሆን አፈናቃዩንም ተፈናቃዩንም በአንድ ላይ የሚያጠፋ፤ የአገርንም ሆነ የግለሰብን ልማት ወደኋላ የሚጎትት የኋላ ቀርነት መገለጫም ጭምር ነው፡፡

በሌላ በኩል ዜጎች ከአንድ አካባቢ ሲፈናቀሉ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ለዓመታት ያፈሩትን ሀብትና ንብረታቸውን ጥለው ነፍሴ አውጭ በማለት ነው የሚሰደዱት፡፡ ይህ ለዓመታት ያካበቱትን ሀብት በቀላሉ ትተው መሰደዳቸው የዘራፊዎችን ጉልበት በማፈርጠም ለሌላ ዘርፊያ  የሚጋብዝ   አገርንም ወደ ፍፁም ደህነት የሚያወርድ እኩይ ተግባር ነው፡፡

በዚህም ሳያበቃ መንግስት ዜጎች ከተፈናቀሉ በኋላ መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገው ጥረት ደግሞ ሌላ የኢኮኖሚ ጫና ነው፡፡ መንግስት እንደ አገር የተደቀነብንን ድህነት ለማስወገድ የሚያደርገውን ጥረት የሚያስፈጓጉል ኢኮኖሚያዊ አቅሙን የሚያዳክም ነው፡፡ በዋናነት ዜጎች የሞላ ቤታቸውን ጥለው በመውጣት በድንገት ወደ ፍፁም ድህነት ሲገቡ የሚኖረውን ማህበረሰባዊ ጫና መገመት አያዳግትም፡፡ የአገርን ምስል የሚያበላሽ ሄዶ ሄዶ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ጭምር በመግታት አገራዊ ሁኔታችንን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከትም ይሆናል፡፡

አገራችን ያላት የተፈጥሮ ሃብት መሬት እንኳንስ ለገዛ ወንድም እህቶቻችን ይቅርና ጦርነትንና የእርስ በእርስ ግጭትን ፈርተው ከተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያን መርጠው ለመጡ ለሌላማ ቢሆን በአግባቡ መጠቀም ከቻልን የሚያንስ ሆኖ አይደለም፡፡

ያ ሁሉ መተሳሰባችን፣ የአለምን ቀልብ የገዛው አብሮነታችንና መቻቻላችን ወዴት ሄደ? የእኔ ይቅርብኝ ብሎ ለተራበ አጉራሽ፣ ለታረዘ አልባሽ የሆነ ምስጉን ህዝባችን እሴት ስለምን በጥቂት ሆደ አደር ሰዎች ይሸርሸር? ዛሬ በሁሉም ጫፍ ያለ ኢትዮጵያዊ ተፈናቃይ ወገኖቻችንን ማቋቋም ላይ ትኩረቱን አድርጓል በእርግጥም ይህች ናት አገሬ……በሃዘን፣ በደስታ አብሮ መኖርን፣ አብሮ መራብን፣ አብሮ መደሰትን ያውቅበታል፡፡ እናም ሁላችንም አብሮነታችንን ማን አየብን ልንል ይገባል…ማን አየብን?