ትኩስ ዜና

‹‹በብዙ ጨለማና አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያ ነጻ ማውጣት የሚችለው እውቀት ብቻ ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከነገ ጀምሮ ስብሰባውን ያካሂዳል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሀገራዊ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ አቋም እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ። ከዛሬ አመት በፊት በኢህአዴግ ውስጥ የተጀመረው ለአብዮት የተቃረበ ሪፎርም በአገሪቱ የነበረውን የፖለቲካ መልክ መቀየር መቻሉን ድርጅቱ ገለጸ፡፡ ኦዲፒ ለአዳዲስ ድሎች እየተዘጋጀ መሆኑን የኦዲፒ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ገለጹ ኢህአዴግ የውስጠ ድርጅት ጥንካሬውን በማጎልበት የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችለውን አቅጣጫ ተቀመጠ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ቁርጠኛ አቋም የተያዘበት ጉባኤ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ/ 10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የአቋም መግለጫ ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ ኢህአዴግ በአጋርነት ለመስራት የሚመርጡት በሳል ህዝባዊ ፓርቲ 10ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ትናንት ነሓሴ 22ቀን 2007 ዓም በመቐለ ከተማ ሲጀመር የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ያደረጉት ንግግር 10ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ‹‹ህዝባዊ አደራን በላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን›› በሚል መሪ ቃል በመቀሌ ከተማ ተጀምሯል፡፡ ጉባኤው ሰፋፊ አቅጣጫዎችንና የእቅድ ግብአቶችን እንደሚያስቀምጥ ተገለፀ

ጉባኤ ጉባኤ

Back

10ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ትናንት ነሓሴ 22ቀን 2007 ዓም በመቐለ ከተማ ሲጀመር የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ያደረጉት ንግግር

10ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ትናንት ነሓሴ 22ቀን 2007 ዓም  በመቐለ ከተማ ሲጀመር  የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ያደረጉት ንግግር  

የተከበራችሁ ጉባኤተኞች፣

የተከበራችሁ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የመጣችሁ ተጋባዥ እንግዶች፣

የተከበራችሁ የውጭ እህት ፓርቲዎች የልኡካን አባላት ክቡራትና ክቡራን፣

ከሁሉ አስቀድሜ በድርጅታችን ኢህአዴግ ለ10ኛ ጊዜ በሚካሄደው ጉባዔያችን እንኳን ወደ ውቢቷ ከተማ መቐለ በሰላም መጣችሁ እያልኩ በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሚና ባለው በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ ለመሳተፍ በመብቃታችንም እንኳን ደስ አለን፣ እንኳን አደረሰን ለማለት እወዳለሁ፡፡

በድርጅታችን መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የኢህአዴግ የመጨረሻው ከፍተኛ የአመራር አካል ድርጅታዊ ጉባዔ ሲሆን ኢህአዴግ እስካሁን 9 መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤዎች አካሂዷል፡፡ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት በመደምሰስ የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸው አካላት የሚሳተፉበት የሽግግር መንግስት የሚመሰረትበትን የመሰረት ድንጋይ ከጣለው የ1983ቱ የተምቤኑ የመጀመሪያ ድርጅታዊ ጉባዔያችን ጀምሮ በድርጅታችን ብሎም በሀገራችንና በአለም የፖለቲካ መድረክ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ አሻራዎችን አስቀምጦና ሀገራችንን በህዳሴ ጉዞ ሃዲድ ውስጥ አስገብቶ ባለፈው ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ መስዋእት ማግስት እስካካሄድነው 9ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ድረስ የተካሄዱት ጉባዔዎቻችን የየወቅቱን የትግል ምዕራፎች ያገናዘቡ ትክክለኛ አቅጣጫዎችንና ውሳኔዎችን ያስቀመጡ ነበሩ።

ካለፉት ጉባኤዎቻችን መካከል በ1993ዓ.ም የተካሄደው 4ኛው ድርጅታዊ ጉባዔያችን ኢህአዴግ በውስጡ የተደቀነበትን የመበስበስና የጥገኛ ዝቅጠት አደጋ እና መገለጫዎች በበቂ ጥናትና ትግል ላይ ተመስርቶ የድርጅቱን የትግል መስመር በማጥራት የተሃድሶ አቅጣጫዎቻችንን በጥራት በማስቀመጥ ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የተሸጋገረበት ታሪካዊ ጉባኤ ነበር። ይኸው ጉባዔ ኢህአዴግ በትጥቅ ትግሉ ወቅት እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ያለፈበትን መድረክ በመድገም የአላማ ፅናትና ህዝባዊ ወገንተኝነት ያለው ድርጅት መሆኑን ዳግም ያረጋገጠበትም ጉባኤ ነበር፡፡ በተሃድሶው ጠርቶ በወጣው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር እየተመራም ባለፉት ተከታታይ 12 አመታት አገራችንን በፈጣንና መሰረተ ሰፊ እንዲሁም የአገራችን ህዝቦች በየደረጃው መጠቀም የጀመሩበት ዕድገትና ልማት በማስመዝገብ  በህዳሴ ጉዞ ወደፊት እንድትገሰግስ አስችሏል።

በ2005ዓ.ም የተካሄደው ዘጠነኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችን በከፍተኛ የአመራር ብቃቱ ድርጅታችንን ለማያቋርጡ ድሎች የሚያበቃ አመራር በመስጠት ቁልፍ ሚና የተጫወተውን ታላቁን መሪያችንን ጓድ መለስ ዜናዊን ባጣንበት ማግስት የተካሄደ ነበር፡፡ ወቅቱ በአንድ በኩል ታላቅ መሪያቸውን ያጡት የአገራችን ህዝቦች በጥልቅ ሃዘን ውስጥ ሆነው "የተጀመረውን ልማትና ዴሞክራሲ በማስቀጠል የታላቁን መሪ ራእይ እናሳካለን" በማለት ቃል ኪዳናቸውን ያደሱበት በሌላ በኩል የጽንፈኛና የጸረ ሰላም ሃይሎች አጋጣሚውን ተጠቅመው አገራችን ለማተራመስ የቋመጡበት ወቅት እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የተካሄደው 9ኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችን "በመለስ አስተምህሮዎች ጠንካራ ድርጅትና የልማት ሃይሎች ንቅናቄ ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ቃል የህዳሴ ጉዟችንን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች በማስተላለፍ የተጀመረውን ልማትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሳይስተጓጎል ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስችሏል፡፡ 10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችን የ9ኛውን ድርጅታዊ ጉባኤ ውሳኔዎችና አፈጻጸም በጥልቀት የሚገመግም እና ቀጣይ እድገትና ዘላቂ ልማት የሚያረጋግጥ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ ይሆናል፡፡

የተከበራችሁ የጉባኤው አባላት፣

የተከበራችሁ ተጋባዥ እንግዶች፣

10ኛውን ድርጅታዊ ጉባዔያችንን የምናካሂደው የህዳሴ ጉዟችንን አጠናክረን ለማስቀጠል ወሳኝ ወቅት ላይ ሆነን ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጉባኤዎች ቁልፍ ትኩረት ሆኖ የነበረውን የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ፈፅመን ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለመተግበር በዝግጅት ላይ ባለንበት ታሪካዊ ወቅት ላይ የሚካሄድ ጉባዔ ነው። የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም በትልቁ ከማቀድ ጀምሮ የአይቻልምን መንፈስ በመስበር ለቀጣዩ የህዳሴ ጉዟችን ከጥንካሬዎቻችንም ሆነ ከድክመቶቻችን በርካታ ልምዶችና ትምህርቶች የተገኙበት ነው፡፡ እቅዱ ከምንጊዜውም በላይ በልማት ሃይሎች ማለትም በድርጅት፣ በመንግስትና በህዝቡ የተደራጀ ንቅናቄ በመፈጸሙ በእቅድ ዘመኑ በአማካኝ ባለሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዝገብ ፈጣኑን የኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠል ችለናል። በአገር ደረጃ በምግብ እህል ራሳችንን የቻልነው በዚሁ የእቅድ ዘመን ባደረግነው ከፍተኛ ርብርብ ነው። በዚህ አጋጣሚ እቅዱን ለመፈጸም በግንባር ቀደምትነት ለተንቀሳቀሱ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና ፈጻሚ አካላት እንዲሁም የልማቱ ዋነኛ ተዋናይ ለሆነው ህዝባችን በኢህአዴግና በእራሴ ስም የላቀ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ የልማታችን አጋር የሆኑ የወዳጅ አገራት መንግስታትንና ፓርቲዎችም እንደዚሁ ታላቅና የከበረ ምስጋናዬን ለነርሱና ለህዝቦቻቸው ለማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡    

የተለጠጠ ግቦችን ይዞ የተዘጋጀውን የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለመተግበር ሳንታክት በመስራታችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ የያዝነው ራዕይ የመሳካቱ ጉዳይ ከወዲሁ እውን እንደሚሆን መታየት ጀምሯል። ይህም ሆኖ በእቅድ አፈጻጸሙ በቀጣይ ልንፈታቸውና ልናርማቸው የሚገቡ ተግዳሮቶችና ድክመቶች ነበሩ፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በተለይ በከተሞች የበላይነቱን እንደያዘ ይገኛል፡፡ ለጉባኤው በሚቀርበው ሪፖርት በእቅድ አፈጻጸማችን የነበሩ ጥንካሬዎችና ድክመቶች የቀረቡ ሲሆን ጉባኤው በጥልቀት ገምግሞ ጥንካሬዎችን አጎልብቶ ለማስቀጠልና ድክመቶችን ለማረም የሚያስችሉ አቅጣጫዎችንና ውሳኔዎችን እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል፡፡

10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችን አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ በስኬት በተካሄደበትና ህዝቡ ለድርጅታችን ከፍተኛ ኃላፊነት በሰጠበት ማግስት የሚካሄድ መሆኑ ሌላው ጉባኤውን ታሪካዊ የሚያደርገው ጉዳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ህዝባችን በምርጫው ያስተላለፈውን ውሳኔ እና ከውሳኔው በስተጀርባ ያስተላለፋቸውን መልዕክቶች በአግባቡ ይረዳቸዋል። ህዝቡ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤትነት መብቱን ተጠቅሞ የሰጠው ውሳኔ ኢህአዴግ ባስመዘገባቸው ስኬቶችና እና በእስካሁን ያልረካባቸው ጉዳዮችም ኢህአዴግ ከህዝባዊ እና አብዮታዊ ባህሪው ተነስቶ ሊፈታቸው ይችላል የሚል እምነት አሳድሮ ያስተላለፈው ውሳኔ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መራጩ ህዝብ ሊመራውና ሊያገለግለው የሚችለውን ፓርቲ በባዶ የተስፋ ቃል ብቻ ሊሸነግለው ከሚፈልገው ፓርቲ የለየበት በሳል ውሳኔ ያስተላለፈበትም ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ በአገራችን መገንባት የተጀመረው የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አሸናፊ ሆኖ የወጣበት በመሆኑ የህዳሴ ጉዟችንን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል ያስቻለ የህዝብ ውሳኔ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጥላቻና የቂም በቀል የዜሮ ድምር ፖለቲካ እየከሰመ ሂዶ የተረጋጋ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ ከ2002ቱ ምርጫ ቀጥሎ ዳግም መሰረቱን ያጠናከረ በሳልና በአርቆ አስተዋይነት የተሰጠ የህዝብ ውሳኔ ነበር፡፡

በዚህ አጋጣሚ ህዝባችን ምክንያታዊ በሆነ በሳል ውሳኔ ሙሉ ድጋፉን ለድርጅታችን በመስጠቱ በድርጅታችን አባላትና በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔያችን ስም ያለኝን ታላቅ ክብርና ምስጋና እንዲሁም አድናቆት ለመግለፅ እወዳለሁ። የህዝባችን በሳል ውሳኔ ለኢህአዴግ የሰጠው ታላቅና ከፍተኛ ኃላፊነትና አደራ በመሆኑ ጉባዔያችን ይህን ከባድ ኃላፊነትና አደራ መወጣት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች እንደሚያስተላለፍ ይጠበቃል፡፡

የተከበራችሁ የጉባኤው አባላት፣

የተከበራችሁ ተጋባዥ እንግዶች፣

ኢህአዴግ የተቀበለው ህዝባዊ አደራ ወገብ የሚያጎብጥና እንቅልፍ የሚነሳ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ለመመለስ የሚያስችለውን ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የእቅድ አቅጣጫዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ባሳተፉ የውይይት መድረኮች በማዳበር አዘጋጅቷል፡፡ 10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔያችን በጥልቀት ከሚመክርባቸውና ውሳኔ ከሚያስተላልፍባቸው አንኳር ጉዳዮች አንደኛውም ይሄው አቅጣጫ ነው። አቅጣጫዎቹ የአገራችንን ራእይ፣ የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ የዘላቂ ልማት ግቦችን እና መሰል ጉዳዮችን እንደመነሻ ወስዷል፡፡ የእቅድ አቅጣጫዎችና ግቦቹ አገራችንን በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የተያዘውን ራእይ እውን ለማድረግ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ልናሳካቸው የሚገቡ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ግቦችን፣ መሰረታዊ አቅጣጫዎችንና የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አካቶ ይዟል። ጉባኤው እቅዱን በጥልቀት በመመልከት አዳብሮ እንደሚያጸድቀው እምነቴ የጸና ነው፡፡

የተከበራችሁ የጉባኤው አባላት፣

የተከበራችሁ  ተጋባዥ እንግዶች፣

ድርጅታችን ባለፈባቸው የትግልና የስኬት መንገዶች ሁሉ መላ የሀገራችን ህዝቦች ከጎኑ በመሰለፍ ወሳኙን ሚና ተጫውተዋል። በዚህም ለዘመናት ወድቀን ከነበረበት የድህነትና የኋላቀርነት አረንቋ እና ተጠፍረን ተይዘን ከነበርንበት አስከፊ የድህነትና የመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ እጦት ወጥመድ ደረጃ በደረጃ እየተላቀቅንና እየወጣን የህዳሴ ጉዟችን በማፋጠን ላይ እንገኛለን። ከፊት ለፊታችን የሚጠብቀን መድረክም የልማት ሃይሎችን የተደራጀ ንቅናቄ በእጅጉ ይጠይቃል፡፡ የአገራችን ህዝቦች የጀመሩት የህዳሴ ጉዞ ከዳር የሚደርሰው በእነሱው ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ባለቤትነት በመሆኑ ከተለመደውም በጠለቀና በነቃ የዜግነት ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚገለጽ በመሆኑ ይህንኑ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ድርጅታዊ ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን፡፡ ድርጅታቸው ኢህአዴግም በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው የመሪነት ሚናውን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ማስተላለፍ የሚጠበቅበት በመሆኑ ይህንን ተልእኮውን በብቃት እንደሚወጣ ለማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ የጉባኤው ተሳታፊዎችም የሀገራችን ህዝቦች ከኛ የሚጠብቁትን መሪነት መወጣት በሚያስችለን ደረጃ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ እምነቴ የፀና ነው፡፡

በመጨረሻም የ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤችን በስኬት እንዲጀመር አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ በተለይም በእንዲህ የደመቀና ያሸበረቀ ሁኔታ የተቀበሉንን የህወሓትና አመራሮችና አባላት እንዲሁም የመቐለ ከተማ ህዝብ በኢህአዴግና በራሴ ስም እያመሰገንኩ ጉባኤያችን ስኬታማ እና ውጤታማ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡   

ህዝባዊ አደራን በላቀ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን!

ዘላለማዊ ክብር እና ሞገስ ለትግሉ ሰማዕታት!

አመሰግናለሁ!!