Skip to Content
   አማርኛ    እንግሊዘኛ    ያግኙን    ሴትች ሊግ    ወጣት ሊግ

Back

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችን እና ያለፉትን ወራት የእቅድ አፈፃፀም በጥልቀት ገምግሞ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ከሚያዚያ 7 - 8 /2011 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ሀገራዊ የለውጥ ሂደቱ ያለበትን ደረጃና የተከናወኑ የፖለቲካና የድርጅት ስራዎችን አፈፃፀም ገምግሟል። ባለፈው አንድ አመት በተለይም 11ኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ ከተካሄደበት መስከረም ወር ጀምሮ የጉባዔውን ዋናዋና ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች መሰረት በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያስቻሉ ተጨባጭ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውን ምክር ቤቱ በዝርዝር ተመልክቷል።

የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ የተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መኖራቸውን፤ እህት እና አጋር ፓርቲዎች እያደረጓቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች በመልካም ጅምርነት የገመገመው ምክር ቤቱ በቅርቡ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተፈረመው የቃል ኪዳን ሰነድ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ ያለው እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ኢህአዴግ የቃል ኪዳን ሰነዱን አክብሮ በመንቀሳቀስ ሃላፊነቱን በተሟላ መልኩ እንዲወጣ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ህገ መንግስቱን፤ የሀገሪቱን ህጎች አክብረው በሰላማዊ የሀሳብ ትግል ብቻ በመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ ውስጥ ያለባቸውን ሃላፊነት ተረድተው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪውን አስተላልፏል።

ከፖለቲካዊ ስራዎች አንፃር ሰፊ ውይይት ከተካሄደባቸው ጉዳዮች
መካከል የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲና የአመራር አንድነት ይገኝበታል። ምክር ቤቱ በእህት ድርጅቶችና በአመራሩ መካከል የሚታየውን መጠራጠር በመፍታት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል። ከዚህ አኳያ መታረምና መስተካከል ያለባቸው ነጥቦች ላይ ፍጹም ነጻ በሆነ መንገድ ሀሳብ እንዲንሸራሸርና በመጨረሻም አገርንና ህዝብን ማዕከል ያደረጉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ተፈጥሯል፡፡

በኢኮኖሚው መስክ የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎች ሀገራዊ የኢኮኖሚ መቀዛቀዙን በማስተካከል ረገድ በጎ ሚና እንደነበራቸው የተመለከተው ምክር ቤቱ በተለይም ሀገራዊ የውጪ ምንዛሬ ክምችቱን በማሳደግ በኩል ትርጉም ያለው ስራ እንደተሰራ ገምግሟል። በዚህ መስክ መሻሻሎች እየታዩ ቢሆኑም ከፍተኛ የስራ አጥነት፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ የብድር ጫና ችግሮች በአግባቡ ያልተቀረፉ በመሆናቸው መዋቅራዊ መፍትሄ ለመስጠት መረባረብ እንደሚገባ ምክር ቤቱ አስምሮበታል።

የወጣቶችን የተሳታፊነትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች በተለይም የስራ አጥነት ችግርን ለመፍታት እስካሁን የተደረጉት ጥረቶች ያሉ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር ፍላጎት አንጻር አሁንም ከለውጡ በሚገባው ደረጃ ያልተጠቀሙበት ሁኔታ መኖሩን ምክር ቤቱ በአጽንኦት ገምግሟል። በተጨማሪም ወጣቶቹ ያሏቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ ጥያቄዎች ገና በተሟላ ሁኔታ አለመመለሳቸውን አይቷል። በመሆኑም የወጣቶች ተጠቃሚነት ጉዳይ በቀሪ የበጀት አመቱ ወራት ልዩ አገራዊ አጀንዳ እና የርብርብ ማዕከል እንዲሆን ምክር ቤቱ ወስኗል።

በየአካባቢው የሚታዩ ከመልካም አስተዳደርና ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚነሱ የህዝብ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተጀመረውን የሪፎርም ስራ አጠንክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ በአጽንኦት ተመልክቷል፡፡

ምክር ቤቱ በፀጥታና ፍትህ ስርዓቱ ላይ የተካሄደው ሪፎርምና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ በመቀልበስ ሀገራዊ አንድነታችንን ለማስጠበቅ የላቀ ሚና እንደነበራቸው በመገምገም የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ያሉ ክፍተቶች መታረም እንዳለባቸውም ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጧል። ከዚህ አንፃር ማንኛውም ለግጭት እና አለመረጋጋት የሚዳርጉ ሁኔታዎች በግልፅ ተለይተው በአስቸኳይ መታረም እንዳለባቸውና መንግስትም ህግን የማስከበር ቁልፍ ሃላፊነቱን በጥብቅ መወጣት እንደሚገባው የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከዚህ አኳያ ክልሎች እና የየአካባቢው መዋቅር የየራሳቸውን ህገ መንግስታዊ ግዴታ እንዲወጡ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ባለፉት ጊዚያት በአንዳንድ አካበቢዎች በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ላይ በጥልቀት የተወያየው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመስለ አስፈላጊውን ጥረት እንዲደረግ አጽንኦት ሰጥቶታል፡፡

ከሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ወዳጅነት መመስረቱና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብር እየተካሄደ መሆኑን የገመገመው ምክር ቤቱ በተለይ ከኤርትራ መንግስትና ህዝብ ጋር የተጀመረው ግንኙነት ሁለቱ ሀገራት ያሏቸውን ባህላዊ፣ የኢኮኖሚዊ እና ማህበራዊ ትስስር የሚያጠናክሩ ዕድሎችን አሟጦ መጠቀም በሚያስችል መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወስኗል።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ለውጡ ሰፊና ህዝባዊ መሰረት ይዞ እንዲቀጥል ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ፍትህን ማረጋገጥ እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትንና ሀገራዊ ክብርን ማረጋገጥ ለነገ የማይባሉ የድርጅቱ ቀዳሚ ተልዕኮዎች መሆናቸውን አስቀምጧል። በመሆኑም እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችንና ድሎችን የሚያሰፋና ጉድለቶችን የሚያርሙ እንቀስቃሴዎች በጊዜ የለንም መንፈስ መፈፀም እንዳለባቸው አቅጣጫ አስቀምጧል።

በዋና ዋና ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ አውታሮች ግንባታ ላይ በጥልቀት የመከረው ምክር ቤቱ እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው በቀጣይ ጊዜ በተለይም ለመስኖ ልማት የሚሰጠውን ትኩረት እንደተጠበቀ ሆኖ በቀሪ ወራት በመኸር ስራ ላይ መረባረብ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ እንዲሁም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሀገራዊ ኢኮኖሚውን የበለጠ ለማነቃቃት መረባረብ እንደሚገባም ዝርዝር አቅጣጫ አስቀምጧል።

የመገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ ለውጡንና ትሩፋቶቹን እንዲሁም ያሉበትን ተግዳሮቶች በተመለከተ በስፋት መዘገባቸው ሀገራዊ አንድነት በማምጣት ረገድ አወንታዊ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ተመልክቷል። ሚዲያው ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁበት መድረክ መሆኑም በአዎንታ የሚታይ ለውጥ ነው ብሏል ምክር ቤቱ። ሆኖም ከኋላው ታሪካችን ትምህርት በመውሰድ የወደፊት ተልዕኳችንን ለማሳካት የሚያግዙ መልዕክቶችን ከመቅረፅ ይልቅ ባለፉት ጉድለቶች ላይ ብቻ በመንጠልጠል ብሶትን ማራገብ የሚታይበት በመሆኑ በቀጣይ መታረም እንደሚገባው አሳስቧል።

ሀሳብን በነጻነት የመግለጽን መብት ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ማህበራዊ ሚዲያው እየተጫወተ ያለው አዎንታዊ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ ዴሞክራሲውን የማቀጨጭ ሚናው እየጎላ መምጣቱን ገምግሞ ከለውጡ ጋር በተዛመደ መልኩ የሚታረምበትን አካሄድ መከተል እንደሚገባ አመላክቷል። የጥላቻ ንግግሮችን በህግ አግባብ መከላከል አስፈላጊ እንደሆነም ምክር ቤቱ አምኖበታል።

ምክር ቤቱ ለውጡን እየተፈታተኑ ያሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተ በስፋት የተወያየ ሲሆን ለዉጡ አሁንም ህዝባዊ መሰረት ይዞ እንዳይጓዝ፤ ከተቻለም እንዲቀለበስ የሚጥሩ ሃይሎች የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን አይቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከጽንፈኛ ብሄርተኝነት፤ ስርዓት አልበኝነት እና የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ፈተናዎች የአገራዊ አንድነታችንን ችግሮች በመሆናቸው በተባበረ ክንድ በመፍታት፤ ለውጡን ማስቀጠልና ማስፋት ለምርጫ የሚቀርብ ሳይሆን የሀገር ህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ከለውጡ በተቃራኒ ያሉ አስተሳሰቦችን መግራትና ተግባራትን መግታት ወቅቱ የሚጠይቀው ቁልፍ ተልዕኮ መሆኑን አስምሮበታል።

በመጨረሻም የኢሕአዴግ ምክር ቤት በቀረበው ሰነድና ሪፖርት ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኃላ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ስለሆነም የኢህአዴግ ምክር ቤት የድርጅቱ አመራር፣ አባላት፣ አጋር ድርጅቶች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበራትና መላው የሀገራችን ህዝቦች የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ በማስቀጠል የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥሪውን ያስተላልፋል።
የኢሕአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት
ሚያዚያ 9ቀን 2011 ዓ.ም


ኢህአዴግ

ኢህአዴግ አገር የመምራት ሃላፊነትን ከተረከበ ጊዜ ጀምሮ ከውስጥም ከውጭም የሚነሱ በርካታ ውጣ ውረዶችን ያስተናገደ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣምና የህዝባችንን ሁለንተናዊ መለወጥ ታሳቢ ያደረገ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ስርዓት በማራመድ በውጭ ሃይል ተፅእኖ የሚጠመዘዝ ድርጅት አለመሆኑን ገና በጠዋቱ በተግባር ያሳየ ድርጅት ነው፡፡

ከደርግ ውድቀት ማግስት አገራችን የመበታተን ስጋት ውስጥ የነበረችበት ሁኔታ ቢኖርም መላ የሃገሪቱን ህዝቦች በማስተባበርና በብስለት በመምራት ዴሞክራሲያዊ አንድነቷ በፅኑ መሰረት ላይ እየተገነባ እንዲዘልቅ አስችሏል። ህገ መንግስታችን የአንድነታችንና የመከባበራችን ማሰሪያ ውል እንዲሆን በሚያስችል መልኩ በህዝብ ሙሉ ተሳትፎ ተቀርፆ በመፅደቁ ያንን የመበታተን ስጋት ተሻግረን በጋራ ለዘላቂ ለውጥ መረባረብ ጀምረናል።

እባክዎን ማንኛውም አስተያየት ካልዎት ክልክ በማድረግ ይፃፉ!

ስለአስተያየትዎ እናመሰግናለን!!!

ዜና ዜና

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች ላይ በመወያየት ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓም ባካሄደው ስብሰባ ባለፈው አንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ ውስጥ የተከናወኑ የብሔራዊ ደህነንት ስኬታማ ስራዎችን እንዲሁም እያጋጠሙ ያሉትን ተግዳሮቶች የገመገመ ሲሆን የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል፡፡ ኮሚቴው የሀገራችንን ብሔራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎችን በጥልቀት የተመለከተ ሲሆን ለአብነትም በውጭ ሀገራት የነበሩ የታጠቁ ሃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር የነበረው ሰላምም ጦርነትም ያልሆነ ግንኙነት መስተካከሉ ከለውጡ በኋላ የተገኙ ስኬቶች መሆናቸውን ግምግሟል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ…

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ማካሄድ ጀምሯል

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) ዛሬ ግንቦት 8ቀን 2011 ዓም ስብሰባውን ማካሄድ የጀመረ ሲሆን በብሄራዊ ደህንነትና ሌሎች ወቅታዊ እየተወያየ መሆን የኢህአዴግ ም/ቤት ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ በአጭር ጊዜዎች ውስጥ በተከታታይ እየተገናኘ ስራዎችን በጋራ እንዲገመግምና አቅጣጫዎችን እንዲያስቀምጥ መግባባት ላይ እንደደረሰ መግለጻችን ይታወሳል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ…

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሞችን በጥልቀት በመገምገም ቀጣይ የኢኮኖሚ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዚያ 28/2011 ዓም ባካሄደው ስብሰባ ያለፉት ዓመታትን የኢኮኖሚ ዘርፍ አፈፃፀም በዝርዝር ከገመገመ በኋላ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሞችን በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል። ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከ2003 እስከ 2010 ዓም በአገሪቱ የተመዘገበውን የኢኮኖሚ አፈፃፀም የገመገመ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በአማካይ የ9.6 እድገት ማሳየቱን በዚህም የግብርና ዘርፍ የ5.7 በመቶ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ የ19.1 በመቶ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፍ 10.3 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ተመልክቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ…

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ማካሄድ ጀመረ

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከዛሬ ሚያዝያ 28ቀን 2011 ዓም ጀምሮ ስብሰባውን ማካሄድ ጀምሯል፡፡ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በድርጅታዊና ወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት በማካሄድ ውሳኔዎችንና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ…

መጣጥፎች መጣጥፎች

እንደገና ወደ ኋላ ለማን በጀ?

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች ላይ የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት የክልሉን ልማት ወደ ኋላ ለመመለስ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት በመተሳሰብና በመቻቻል አብሮ ከኖረው ከወንድሙ የኦሮሞ ህዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻከርና እርስ በእርስ የጥርጣሬ መንፈስ እንዲፈጠር በማድረግ የመተባበርና የመደጋገፍ አቅሙን ለማዳከም ታልሞ የተሰራ ሴራ ነው፡፡ በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተጀማመሩና የኢኮኖሚ ምህዋሩን አንድ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችሉ ልማቶችን ከመደገፍና ደጀን ከመሆን ይልቅ ኢ-ምክንያታዊ በሆኑ ነገሮች ሰበቦችን በመፍጠር ብሔርን መሰረት አድርገው ሁከትና አለመረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች መንግስትን የማዳከም ስራ ላይ ተጠመደዋል፡፡ የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ የህዝብና መንግስት ንብረቶችን ማውደም፣ እንዲሁም ይህንኑ ግርግር መነሻ በማድረግ በዝርፊያና ስርቆት ወንጀሎች ላይ በመሰማራት በህገ ወጥ መንገድ የግል ሀብታቸውን ለማፍራት የሚኳትኑ ጥቂት እፉኝቶች የሌት ተቀን ስራቸው አድርገውታል፡፡

ለሚወረወርልን እሳት ጭድ እየመገብነው ነው ወይስ ውሃ እየቸለስንበት?

በዚህ ይህ የኔ አካባቢ ነው፣ አንተ መጤ ነህ፣ ውጣልኝ/ውጭልኝ እስከ መባባል ተደርሶ፤ የሰው ህይወት እየጠፋና በርካቶች ለዘመናት ከኖሩበት የትውልድ ቀዬአቸው እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ይህ ግጭት እውነትም በህዝቦች መካከል እየተፈጠረ ያለ ግጭት ነው ወይ? ሲባል ሁሉም አፉን ሞልቶ በጭራሽ፤ እንዴት ተደርጎ፤ በተድላ ጊዜ በደቦ አመርተን ለአገር የምንተርፍ፣ በችግራችን ጊዜ ደግሞ አንድ ቂጣ ተካፍለን በልተን አድረን ክፉ ደጉን አብረን ያሳለፍን፤ አንድ እናት ገቢያ ስትሄድ የአንዷን እናት ጡት ለሁለት ጠብተን ያደግን ሰዎች ምን ቆርጦን ጦር እንማዘዛለን? እንላለን፡፡ ከግጭት መልስ በየአካባቢው የሚደረዱ ህዝባዊ ውይይቶች ላይም አዘውትረን የምንሰማው ይህንኑ ነው፡፡ ደግሞም ሀቅ ነው፡፡ ታዲያ ምንድነው የሚያጋጨን? ሲባል መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ያንን አብሮነታችንን አፍርሶ እርስ በእርስ አባልቶ ሊያጣፋን የሚሻ የጋራ ጠላታችን ወይም በግጭት ውስጥ ጥቅም የሚፈልግ ቁንጽል ፖለቲከኛ ወይም ብሄሩን መደበቂያ አድርጎ ከተጠያቂነት ለመሸሽ ላይ ታች የሚል ሌባ/ሙሰኛ ነው፡፡ ሲጠቃለል ግን የኛም ሆነ ከውጭ የመጣ ወገንን ደም በማቃባት ትርፍ የሚፈለግ ወይም የሚደሰት ያው ጠላታችን ነው፡፡

አብሮነታችንን ማን አየብን?

ኢትዮጵያ ሰላም ያለባት ሀገር እየመሰለች፤ ነገር ግን በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያውን ቁጥር ከመያዝ ባሻገር በዚህ በኩል በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሱ ካሉት ሶርያ፣ ሶማሊያ፣ የመንና ደቡብ ሱዳን ጋር አብሮ ስሟ መጠራቱ ለኢትዮጵያዊ ማንነት የማይመጥን የአብሮነትየመደጋገፍ ባህላችንን የሚያጠለሽና በሁላችንም ዘንድ በእጅጉ ሀዘኔታን የሚፈጥር ነው፡፡

ከ‹‹እኔ ብቻ›› ስሜት መሻገር ይገባል!!

በመደመር እሳቤ የጀመርነው ሁሉን አቀፍ አገራዊ ለውጥ እንደ ንብ ታታሪ ሆኖ በመስራት ለውጡን ዳር ማድረስ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ሀላፊነት ነው፡፡ በእኛነት ስሜት በመደራጀት በአገራችን ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በጋራ በመታገል ዛሬ የደረስንበት ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል፡፡ በተባበረ አንድነታችን ያቀነቀንለት የለውጥ ዝማሬ አልፎ አልፎ አንዳንድ መሰናክሎች እያስተናገደ ይገኛል፡፡ በቁልቁለት መንገድ ለማስገባት ከኋላ የሚገፉ ከፊት የሚስቡ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሯራጡ ሃይሎች እዚም እዚያም ይስተዋላሉ፡፡ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ወደ ኋላ ለመመለስ በርካታ ወጥመዶች እየዘረጉ ይገኛሉ፡፡ በብሄሮች መካከል ያለውን ልዩነት በማጉላት በሕዝቦች መካከል ጭቅጭቅና ንትርክ ለመፍጠር የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ በበርካታ ውጣውረድ ታልፎ የተገኘውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ችግሮችን በሠለጠነ እና በሰከነ መንገድ በመፍታት የዴሞክራሲ ባህላችንንም ማሳደግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

የፌዴራል ስርዓቱ ሁሉንም ፍላጎቶች ማስተናገድ የሚችል ነው!

እነአሜሪካና ስዊዘርላንድ ፌዴራላዊ ስርዓትን ተቀብለው መተግበር ከጀመሩ ምዕተ አመት አስቆጥረዋል። እንደተባለው ስርዓቱ ሀገርን አደጋ ውስጥ የሚጥልና አንድነትን የሚያጠፋ ቢሆን ኖሮ ዛሬ አሜሪካም ሆነ ስዊዘርላንድ የሚባሉ አገራትን ላናይ እንችል ነበር። አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ1789 በህገመንግስት የተረጋገጠ ፌደራላዊ ስርዓትን በሀገሯ ላይ እውን አድርጋለች። ስዊዘርላንድ ደግሞ እ.ኤ.አ በ1848 ስርዓቱን በህገመንግስቷ እውቅና ሰጥታ ዘርግታለች። ጀርመንም እ.ኤ.አ.በ1871 ፌዴራላዊ መንግስትን ይፋ አድርጋለች። በመቀጠልም ካናዳ፣ ቤልጂየም፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የተለያዩ ግዛቶች፣ ቼኮስሎቫኪያ፣ ከኮሚኒዝም መፈራረስ በኋላ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ወደ ፌዴራል ስርዓት በሂደት እንደተቀላቀሉ የዘርፉ ምሁራን ከጻፏቸው ሰነዶች መረዳት ይቻላል።

ራዕይ ራዕይ

ተልዕኮ ተልዕኮ

እሴቶች እሴቶች

© 2019 (ኢህአዴግ) የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር.