Back

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዶ/ር አብይ አህመድን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰየመ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 3ኛ ዘመን 2ኛ ልዮ ስብሰባ ዶ/ር አብይ አህመድን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር አድርጎ ሰየመ፡፡ ዶ/ር አቢይ አህመድ በምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሰየሙ በኋላም ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡

ተመራጩ ጠቅላይ ሚንስትር ውጤት ያመጡ አሰራሮች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንና ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ማማሻያ በማድረግ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ይሰራል ብለዋል፡፡
የስልጣን ሽግግሩ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ መጀመሪያ በመሆኑ መንግስት በአዲስ እይታ እድሉን ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል፡፡
ፍትህ ብልፅጽግና እንዲሰፍን ይሰራልም ብለዋል፡፡ ከስህተቶቻችን ተምረን ፖለቲካዊ መረጋጋትና የተሻለች አገር ለመገንባት ትኩረት እንደሚሰጥና ለአንድነቷ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡

በአገሪቱ በተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የተፈጠረውን ኢኮኖሚያዊ መቀዛቀዝን ለማካካስ ከመደበኛ የስራ ሰዓት ውጭ በመስራት ጭምር ጥረት ይደረጋል፣ ለዚህም ሁሉም ሊተባበር ይገባል ብለዋል፡፡የወጣቶችና ሴትች ተጠቃሚነት ፣ ጥራት ያለው የትምህርት ስርዓት ማረጋገጥ፣በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ ከመንግስት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ትኩረት መሰጠቱንና ሌሎች ጉዳዮችንም በንግግራቸው አንስተዋል፡፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎችም የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት ሂደት ገንቢ ሀሳብ እያቀረቡ ከመንግስት ጋር ከመቸውም ጊዜ በላይ በጋራ እንዲሰሩ ፍላጎት መኖሩንም አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያና ኤርትራ ለዓመታት የነበረው አለመግባባት መቋጫ እንዲያገኝ መንግስት አበክሮ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል፡፡ ከቅርብ አመታት ወዲህ በሃገሪቱ ለተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የመፍትሄ አካል ለመሆንና የሃገርን ክብርና ብሄራዊ ጥቅምን በተሻለ ሁኔታ ለማረጋገጥ ምሳሌ በሆነ መልኩ ስልጣናቸውን ላሸጋገሩት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢህአዴግ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በመያዝ ሃገሪቱን በመራባቸው አመታት መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት ህገ መንግስታዊና ፌደራላዊ ስርዓት መገንባቱን አንስተዋል። አሁን ላይም ከተመዘገቡ ስኬቶች ባለፈ ላልተሳኩ እቅዶች በአትኩሮት መስራት እንደሚገባም ጠቅሰዋል። ሃገሪቱን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ በማሸጋገር አንድነቷን ጠብቃ የምትቆይበትን መንገድ እያረጋገጡ መሄድም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፤ ፈተናዎችን ወደ እድልና መልካም አጋጣሚዎች በመቀየር መጠቀም እንደሚገባም በመጠቆም።

ኢትዮጵያ በርካታ ዘመን የሚሻገር ታሪክ ያላት ሃገር  ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢትዮጵያውያን ህብረት ጠላቶችን በማንበርከክ ዛሬ ላይ ያደረሰና ለሌሎች ህዝቦች የነጻነት ትግል አርዓያ መሆኑን አስረድተዋል። 

መላው የሃገሪቱ ህዝቦችም ልዩነታቸውን አቻችለው አንድነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፤ በልዩነት ውስጥ መደማመጥና በመርህ ላይ መግባባት ሲቻል የሃሳብ ልዩነት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራልም ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ዴሞክራሲ ማስፈን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፥ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተለይም፥ ሃሳብን የመግለጽ፣ የመሰባሰብና የመደራጀት መብቶች በህገ መንግስቱ መሰረት ሊከበሩ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ለዜጎች ነጻነት እውቅና የሰጠውን ህግ መንግስታዊ ስርዓት በአግባቡ መተግበርና ማክበር እንደሚገባም አንስተዋል።

በመደማመጥ የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድም በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው መርህ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት በንግግራቸው።

ዜጎችም ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጠናከር የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።  ሀገሪቱ ስር የሰደዱ ችግሮች እንዳሉባት በማንሳት፥ በተለይም የዳበረ ዴሞክራሲ አለመኖር፣ ስር የሰደደ ድህነት፣ የተደራጀ የሙስና እና ብልሹ አሰራር መስፋፋት እና የመልካም አስተዳደር እጦት ዋና ዋና መሆናቸውን አንስተዋል።

ዜጎች በሀገራቸው ከቦታ ቦታ የመዘዋወር እና ሀብት የማፍራት መብታቸው መከበር አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እንደዚህ ዓይነት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንዲያበቃ እና ዳግም እንዳይፈጠር መስራት አለብን ብለዋል።

የሁሉም ድምጽ የሚሰማበት ሁሉንም የሚያሳትፍ ዴሞክራሳያዊ ስርዓት የመገንባት ሂደቱን ማጠናከር ይገባልም ብለዋል በንግግራቸው። በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥም መንግስት የዜጎችን መብቶች ለማክበርና ህግን ለማስከበር በጽናት እንደሚሰራ ጠቅሰው፥ ዜጎችም በሰላማዊ መንገድ መብቶቻቸውን ሊጠይቁ እንደሚገባ አንስተዋል።

በዴሞክራሲ ስርዓት የሚታዩ ክፍተቶችን ለማሻሻልም አስፈላጊው ማሻሻያ ይደረጋል ብለዋል፤ ከሁሉም በፊት ሰላም የሁሉም መሰረት በመሆኑ ለሰላም መስራት ይገባል በማለት።

የውጭ ግንኙነት በተመለከተም ኢትዮጵያ የበርካታ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ተቋማት መስራችና መቀመጫ እንደመሆኗ፥ በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተን ፖሊሲ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ከአፍሪካውያን ሃገራት ጋርም በጋራ እንሰራለን ብለዋል፤ ከዚህ ባለፈም ከኤርትራ መንግስት ጋር ለአመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እልባት ያገኝ ዘንድ እንዲያበቃ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

ለሁለቱ ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ሲባልም ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት መንግስት ያለውን ዝግጁነት ገልጸው የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም እንዲይዝ ጠይቀዋል።

ሙስናና እየተስፋፋ የህዝቡ የቅሬታ ምንጭ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር አብይ ይህን ሂደት ለመከላከል መረባረብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከዚህ አንጻርም የተደራጀ ሙስና እና የሃብት ምዝበራን በመመከት ወቅቱ የፈጠረውን ልዩ አጋጣሚ በመጠቀምና ሃገራዊ አቅምን በማቀናጀት ለጋራ ብልፅግና መስራት እንደሚገባም ነው ያነሱት። ባለፉት ጊዜያት በተሰራ ስራ በተመዘገበው ሃገራዊ እድገት በሰው ሃይል ልማት ግንባታ በድህነት ቅነሳ መሰል ዘርፎች ስኬቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።

የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማበረታታት፣ የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማ ለማድረግ፣ የፋይናስ አገልግሎቱን ተደራሽነትና አካታችነት ለማስፋት፣ የስራ እድል ለመፍጠር፣ የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ ለማሳደግና ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የፖሊሲ እርምጃዎች ተወስደዋልም ብለዋል። ይሁን እንጂ የኢኮኖሚ እድገቱንና የማክሮ ኢኮኖሚውን የሚፈታተኑ ችግሮች ተከስተዋል ነው ያሉት፤ የዋጋ ንረት፣ የውጭ ንግድ አለማደግ፣ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን፣ የውጭ እዳ ጫና፣ ኑሮ ውድነት እና የሃገር ውስጥ ቁጠባና ኢንቨስትመንት መካከል ያለው ልዩነት መስፋት ችግሮች እንደነበሩም ነው የገለጹት።

በግብርናው ዘርፍ አበረታች ስራ ቢሰራም በተገቢው ሁኔታ በቴክኖሎጅ መደገፍ ባለመቻሉ መገኘት ያለበት የኢኮኖሚ ትሩፋት አለመገኘቱንም አንስተዋል። ለተከሰቱ ችገሮች ሁሉ የመፍትሄ ቁልፍ በሆነው የትምህርት ዘርፍ ከእድገትና ጥራት ጋር በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

እነዚህንና ሌሎች ችግሮች ለመቅረፍ የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእስካሁን አፈጻጸም በመገመግም አስፈላጊ የፖሊሲ እርምጃ በመውሰድ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ እንደሚሰራም ኢቢሲና ፋና ቢሲ ዘግበዋል፡፡


ኢህአዴግ

ኢህአዴግ አገር የመምራት ሃላፊነትን ከተረከበ ጊዜ ጀምሮ ከውስጥም ከውጭም የሚነሱ በርካታ ውጣ ውረዶችን ያስተናገደ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣምና የህዝባችንን ሁለንተናዊ መለወጥ ታሳቢ ያደረገ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ስርዓት በማራመድ በውጭ ሃይል ተፅእኖ የሚጠመዘዝ ድርጅት አለመሆኑን ገና በጠዋቱ በተግባር ያሳየ ድርጅት ነው፡፡

ከደርግ ውድቀት ማግስት አገራችን የመበታተን ስጋት ውስጥ የነበረችበት ሁኔታ ቢኖርም መላ የሃገሪቱን ህዝቦች በማስተባበርና በብስለት በመምራት ዴሞክራሲያዊ አንድነቷ በፅኑ መሰረት ላይ እየተገነባ እንዲዘልቅ አስችሏል። ህገ መንግስታችን የአንድነታችንና የመከባበራችን ማሰሪያ ውል እንዲሆን በሚያስችል መልኩ በህዝብ ሙሉ ተሳትፎ ተቀርፆ በመፅደቁ ያንን የመበታተን ስጋት ተሻግረን በጋራ ለዘላቂ ለውጥ መረባረብ ጀምረናል።

እባክዎን ማንኛውም አስተያየት ካልዎት ክልክ በማድረግ ይፃፉ!

ስለአስተያየትዎ እናመሰግናለን!!!

አዲስ ራዕይ አዲስ ራዕይ

ቪዲዮ ቪዲዮ

ራዕይ ራዕይ

ተልዕኮ ተልዕኮ

እሴቶች እሴቶች

ጎብኝዎች ጎብኝዎች

Today       

872

       የዛሬ ጎብኚ

Yesterday       

5826

       የትናንት ጎብኚ

This Month       

43884

       የዚህ ወር ጎብኚ

This Year       

196042

       የዚህ ዓመት ጎብኚ

Total        

300616

       አጠቃላይ ጎብኚ