ዜና ዜና

Back

ኢህአዴግና ሀገር አቀፍ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት፣ ክርክርና፣ ድርድር ለማድረግ በሚያስችላቸው ደንብ ረቂቅ ላይ ቀጣይ ውይይታቸውን ዛሬ አደረጉ፡፡

ኢህአዴግና 21 ሀገር አቀፍ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሀገሪቱ አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል በቀጣይ የሚያደርጉትን ውይይት፣ ክርክርና፣ ድርድር አካሄድ ለመወሰን በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ቀደም ብሎ ውይይት መጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን ዛሬም በዚሁ ረቂቅ ደንብ ላይ የሚያደርጉት ውይይት ቀጥሎ ተካሄዷል፡፡
በዛሬው የፓርቲዎች የጋራ መድረክ በረቂቅ ደንቡ ላይ በተካተቱ ጭብጦች ላይ ውይይት በማድረግ ጉዳዮቹን የጋራ ማድረግ የሚያስችላቸውን መግባባት ፈጥረዋል፡፡ የድርድርና ክርክር ተሳታፊ ፓርቲዎች፣ የፓርቲ ተወካዮች ብዛት፣ ምልዓተ ጉባኤና ውሳኔ አሰጣጥ እና የክርክርና ድርድር አመራር የሚሉት አራት ጭብጦች ውይይት የተደረገባቸው ናቸው፡፡
የድርድርና ክርክር ተሳታፊ ፓርቲዎችን በተመለከተ መድረክ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ በመሆኔ ከኢህአዴግ ጋር ዋነኛ ተከራካሪና ተደራዳሪ መሆን አለብኝ የሚል ክርክር መነሻ ሃሳብ ቢያቀርብም በተወያዮቹ ፓርቲዎች ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ በመሆኑም በአብዛኛዎቹ ፓርቲዎቹ የቀረበው ሁሉም ፓርቲዎች በድርድርና ክርክር ተሳታፊ መሆን ይገባቸዋል የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
የ22ቱ ፓርቲዎች የየግል ተሳትፎ እንደተጠበቀ ሆኖ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ ቡድን ፈጥረው ከኢህአዴግ ጋር መከራከርና መደራደር እንደሚችሉም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ የጋራ መድረኮች ከተጠናቀቁ በኋላ ፓርቲዎች በተናጠል ጉዳይ ላይ ከኢህአዴግ ጋር መወያየትና መደራደር ከፈለጉ ለመወያየትና ለመደራደር ዝግጁ ስለመሆኑ በኢሕአዴግ በኩል የቀረበው ተነሳሽነትም በተወያዩቹ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
ፓርቲዎቹ በሚከራከሩና በሚደራደሩበት ወቅት እያንዳንዳቸው ሁለት ተወካዮችን የሚልኩ ሲሆን ተቃዋሚዎች ተደራጅተው በሚቀርቡበት ጊዜ ደግሞ ቁጥራቸው እንደሁኔታው የሚወሰን ይሆናል፡፡ ምልዓተ ጉባኤና ውሳኔ አሰጣጥ በተመለከተ ሁሉም ፓርቲዎች በተናጠል ከኢህአዴግ በጋራ በሚያካሄዱት ውይይት 2/3 ፓርቲዎች መገኘት ሲኖርባቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተደራጅተው ከኢህአዴግ ጋር በሚያደርጉት የሁለትዮሽ ግንኙነት የሁለቱ ተወካዮች በተገኙበት ይካሄዳል፡፡
ፓርቲዎቹ በቀሪ የረቂቅ ደንቡ ጭብጦች ላይ ለመወያየት ለመጋቢት 09 ቀን ቀጠሮ ይዘዋል፡፡