ዜና ዜና

እድሉን እንጠቀምበት

     "በውብዓለም ፋንታየ"                             
ኢህአዴግ የአመራር ለውጥ ካካሄደ በኋላ ባለፉት ጥቂት ወራት የለውጥ ጅማሮዎች  ታይተዋል፡፡ በአመራር ለውጡ ወቅት የተነገሩትን ቃላት በድርጊት ለመመንዘር ቀን ቀንን እስኪተካ መጠበቅ ሳያስፈልግ በየቀኑ ከሚታሰበው እና ከተለመደው በተለየ መልኩ ሁነቶች ተበራክተው፤ አዳዲስ ክስተቶች ተነባብረው ግርምት እና ስለ መጪው ጊዜ ተስፋን ጭሯል፡፡ ይህ ህዝብ እና አገር ተስፋ የጣለበት ለውጥ ጉልበት እንዲኖረው እና ሰፊ ህዝባዊ መሰረት አግኝቶ እንዲደላደል ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ህዝቡ አረጋግጧል፡፡ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ስለ አንድነት፤ ስለ አገር ክብር፤ ስለ መጻይ እድላችን ታላቅነት ከለውጡ ብልጭታ በመረዳት ለለውጥ ሂደቱ ድጋፍ ተችሮታል፡፡
ይህ የለውጥ ሂደት እና ጅማሮ ለአገራችን እና ለዜጎች ይዞ የመጣው በረከት እና ብሩህ ተስፋ በድንበር ሳይወሰን ለቀጠናውም በእጅጉ የሚተርፍ መሆኑን የባለፉት ሳምንታት ክስተቶች ያመላክታሉ፡፡ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማስፈን የሚያስችል አኩሪ ተግባር ተከናውኖ፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጀምሯል፡፡
በአገር ደረጃ ከኢኮኖሚ ጀምሮ የተወጠኑ እቅዶች እና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የዜጎችን ልብ በሀሴት የሚሞላ እና መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውን በእጅጉ እንዲናፈቅ አድርጓል፡፡ በይቅርታ እና በመደመር መንፈስ አንድ አገር ለመገንባት ሲባል የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ጀምሮ የአገርን ህልውና የሚፈታተኑ እንደ ሙስና ያሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመግታት ብሎም ተገቢ እና ህጋዊ የአሰራር ስርዓቶችን የሚተግብሩ፤ ቀውስ ሲከሰት የሚናጡ ሳይሆኑ ተቋቁመው ህዝብ እና አገርን ሊያሻግሩ የሚችሉ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት መጠነ ሰፊ የሪፎርም ስራዎች እየተካሄዱ መሆኑም መጪውን ጊዜ ከምንም በላይ አጓጊ ያደርገዋል፡፡ ከየአቅጣጫው ለዚህ የለውጥ ጅማሮ እየተሰጠ ያለው ድጋፍ እና ትብብርም ይህንን የለውጥ ዘመን ፍሬያማ ለማድረግ ከፍተኛ መሻት መኖሩን ሚያመላክት ነው፡፡ አንድ የለውጥ ሂዳት በሕዝቡ ተቀባይነት ሲያገኝ ደግሞ ለመሪዎች ስንቅ እና ጉልበት፤ ትውልድ ደግሞ በታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራውን እንዲያሳርፍ እድል የሚሰጥ ነው፡፡
በለውጡ የታለመው ዓላማ ከግብ ይደርስ ዘንድ ከሚደረገው ድጋፍ እና ጥረት በተቃራኒው ይህንን አድማሰ ሰፊ ውጥን እና እይታ ለመጋረድ እና ለመበጥበጥ ጥረት መኖሩን በነዚህ ጥቂት ወራት ውስጥ ተመልክተናል፡፡ ግጭት፤ ዜጎችን ማፈናቀል እንዲሁም ህገወጥ የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ዝውውር የወቅቱ ተግዳሮት ሆነው ከለውጡ በተቃራኒ ብቅ ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል በሀዋሳ፤ ወልቂጤ፤ደብረማርቆስ አሁን ደግሞ በባሌ፤ በደንብ ዶሎ፤ በጭናክሰን፤ በምኤሶ ክቡር የሆነው የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንበረት ወድሟል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በለውጥ ዘመናችን መርሆዎች በፍቅር፤ ይቅርታ እና በመደመር የተሸለ ነገን እና የበለጸገች አገርን ስለመገንባት እያማተርን፤ በሁሉም መስክ ስለ ማትረፍ እያሰብን በዚህ ወቅት የህይወትም ሆነ የሌላ ኪሳራ በምንም መልኩ ልናስተናግድ አይገባም ነበር፡፡ የእነዚህ ክስተቶች እውነታ ግን ይህንን የለውጥ ግስጋሴ ለማደናቀፍ በለስ ከቀናም ይህንን የለውጥ ሻማ ለመንጠቅ ወይም ለመቀልበስ ያሰፈሰፈ፤ ከለውጡ እና ከህዝብ ጥቅም በተቃራኒው የቆመ አካል መኖሩን ያመላክታል፡፡
የማንነት ጥያቄዎችን ተገን አድርገው የሚነሱ አተካራዎች እና ሌሎች በቀላሉ ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በማቀናበር፤በይቅርታ እና በፍቅር ዘመን ሌላውን ስለማሳደድ የሚሰብኩ ወይም በሌሎች ላይ ጣትን የሚቀስሩ አንዳንድ ግለሰቦች፤ ቡድኖች እንዲሁም ሚዲያዎች አሁንም መኖራቸው የሚካድ አይደለም፡፡ እዚህም እዚያም እየተከሰተ ያለው አለመረጋጋት ከፊትለፊታችን የተጋረጠውን የችግር ተራራ ለመናድ የሚያስችለንን ጉልበት፤ ጊዜ እና ኃብት በማይረቡ አተካራ እና ነቆራ እንድናባክን በየቦታው ጥረት መኖሩን ያሣያል፡፡ ይህ የለውጥ ሂደት ደግሞ የታለመውን ግብ ለማሳካት ከፊት ለፊቱ የተጋራጡ እነዚህ ተግዳሮቶችን ማለፍ ግድ ይለዋል፡፡
በመሆኑም መላው ህዝባችን በህግ እና ስርዓት በመመራት እንዲሁም ነገሮችን በአስተውሎት በማጤን ለውጡን ለማደናቀፍ እና የፈጠራ ወሬ በመንዛት እርስ በእርስ ሊያዋጋ የሚኳትነውን የክፋት መልዕክተኛ በቃ ሊለው እና ሊያሳፍረው ይገባል፡፡ ለማንም የማይበጀውን እኩይ አስተሳሰብ እና ተግባር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እንዳሉት ስለ አገራችን መጻይ እድል እና ስለ እንድነታችን ሲባል ባለመጋራት ሊናመክነው ይገባል፡፡ አሁን እጅግ የበዛን የለውጥ ባለቤቶች እና ደጋፊዎች እንዲሁም ጥቂት ከክፋት እና ጥፋት መላቀቅ ያልቻሉ ጥቂት አካላት በዚህ የታሪክ ምዕራፍ እና ገጽ ላይ ተገኝተናል፡፡ ወርቃማ ታሪክ ለመጻፍ  እና እነዚህ ክፉ አሳቢዎችን ድል የመንሳት ዕድል በእጃችን ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን ዕድል እንጠቀምበት፡፡ ሰላም!