ዜና ዜና

የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ የአገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ሆኖ ለመንቀሳቀስ መወሰኑ ተገለፀ

በመቐለ ከተማ እየተካሄደ ባለው 4ኛ የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ መደበኛ ጉባኤ የሰላም ጉዳይ የሊጉ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ የነበረ ሲሆን ሊጉ አባላቶቹንና መላውን የኢትዮጵያ ሴቶች በማነቃነቅ ለሰላም ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡ 

አጠቃላይ በሰላም ዙሪያ የሴቶች ሚና ምን መሆን አለበት፤ አሁንስ በአገሪቱ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ምን ይመስላል በሚል የመነሻ ፅሁፍ በኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ሊቀመንበርና የሰላም ሚኒስቴሯ ጓዲት ሙፈርህያት ካሚል ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ሴቶች በአገሪቱ የሰላም እጦት በተከሰተበት ጊዜ ሁሉ ግምባር ቀደም ተጎጂዎች መሆናቸውንና ይህ ሁኔት በአፋጣኝ እልባት ማግኘት እንደሚገባው የሊግ አባላት የጋራ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

የህብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች እንደ አገር ከቤታቸው ጀምረው አጠቃላይ ማህበረሰባዊ ተፅእኖ በማሳደር አስተማማኝና ለሴቶች የተመቸች አገር ለመፍጠር ተግተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡

በውይይቱ ሁሉም የሊግ አባላት ሴቶች ከራሳቸው ጀምረው በአካባቢያቸው ለሰላም እጦት መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በማጤንና በመታገል እንዲሁም የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ ጭምር መታገል እንደሚገባቸው በውይይቱ ተጠቅሷል፡፡ 

ውይይቱ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን የሊጉ አባላት የኦዲትና ቁጥጥር ሪፖርት ላይ ውይይት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ጉባኤው ሊጉን በቀጣይ የሚመሩ አመራሮችን በመምረጥ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡