የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ወጣቶች ሊግ 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በደማቅ ሁኔታ በባህር ዳር ከተማ ተጀምሯል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የድርጅቱ ነባር ታጋዮችን ጨምሮ በርካታ የክብር እንግዶች የተገኙ ሲሆን ለተተኪ ወጣት አመራሮች ልምድ አዘል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጉባኤው በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ውስጥ ተፋፍሞ ለነበረው ለውጥ መቀጣጠል ቁርጠኛ በመሆን ትልቅ አስተዋፆ ላበረከቱት ለቀድሞው የኢህአዴግ እና የአዴፓ ስራ አስፈፃሚ አባል እና የኢህአዴግ ምክር ቤት አባል ለጓድ ተስፋዬ ጌታቸው የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን የሊጉ ጉባኤ እንደ ድርጅት የተፈጠረውን ለውጥ ማስቀጠል እንዲቻል ከፍተኛ ቁርጠኝነት የታየበት ነበር።

አስቀድመው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት ጓድ ምግባሩ ከበደ በመልእክታቸው ላይ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መጎልበት ለኢትዮጵያም ሆነ ለአማራ ህዝብ ህልውና ጠቃሚ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የክልሉ አመራር በልማት እና በዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎች ላይ ለክልሉ ህዝብ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንዳይችል የጥፋት እሳቶችን በመጫር አመራሩ ጊዜውን ክልሉን በማረጋጋት ላይ ብቻ ተጠምዶ እንዲያሳልፍ ለማድረግ እና ድርጅቱ በህዝቡ ዘንድ ያገኘውን መልካም አመኔታ ለማጠልሸት ለውጡን የማይፈልጉ አካላት በእኩይ ተግባር ላይ ተሰማርተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችም ይህንን እኩይ ተግባር አጥብቀው መኮነን እንዳለባቸው እና ከስሜታዊነት ወጥተው ነገሮችን በእርጋታ በመመልከት መስዋእት ለከፈሉለት ለውጥ ዳግም አለኝታነታቸውን እንዲያስመሰክሩ ጠይቀዋል።

ይህንንም ተግባር በበላይነት በመምራት እና በማስተባበር ትልቁን ድርሻ ሊወጣ የሚገባው የአዴፓ ወጣቶች ሊግ መሆኑን ያስገነዘቡት ጓድ ምግባሩ ከበደ በቀጣይም ያላቸውን በሳል የትግል ልምድ ለተተኪ ወጣቶች እንደሚያካፍሉ ለጉባኤው ታዳሚዎች ቃል ገብተዋል።

ከጓድ ምግባሩ በተጨማሪ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዴፓ ወጣቶች ሊግ እና የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር የሆኑት ጓድ ሙቀት ታረቀኝ ሲሆኑ በመልእክታቸው ላይ ወጣቶች ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረላቸውን ለውጥ በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ መንግስትን መሞገት እንዲችሉ እና ክልሉን እና ሀገራችን ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የሚደረገውን ትግል በቆራጥነት እንዲቃላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም የለውጡ አመራር ለተተኪ ወጣቶች ልምዱን እንዲያካፍል እና በበሳል አመራር ተተኪ ወጣቶችን እንዲገራ በአዴፓ ወጣቶች ሊግ ስም ጠይቀዋል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ወጣቶች ሊግ፣የሀረሪ ወጣቶች ሊግ፣የአዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ፣የቤጉህዴፓ ወጣቶች ሊግ፣የድሬዳዋ ወጣቶች ሊግ፣የደኢህዴን ወጣቶች ሊግ ተወካዮች ከመላው የአማራ ክልል ህዝብ እና ከአዴፓ ወጣቶች ሊግ ጋር በጋራ በመሆን ሀገራዊ ለውጡን እክል እንዳይገጥመው በጋራ እንደሚንቀሳቀሱ የአጋርነት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተለይም የቤንሻንጉል ጉምዝ ህዝቦች ዴሞክራሲ ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ተወካይ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ሁለቱን ክልሎች ማእከል በማድረግ በህዝቦች አንድነት መሀል ጥቁር አሻራ ለማሳረፍ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች መኖራቸው እና ይህም እኩይ ተግባር በእንጭጩ እንዲቀጭ በሁለቱም ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በከፍተኛ ሀላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል።