ወጣትነት ለሀገር ግንባታ

ዘላለም ሲሳይ
ወጣትነት ብዙ ተግባራትን የሚፈጸምበትና ሃላፊነት የሚበቃበት የእድሜ ክልል ነው ፡፡ ወጣትነት ኃይል ነው፤ ጉልበት፤ጥንካሬና ብርታት ነው፡፡ በየዘመናቱ ለተመዘገቡ ለውጦችም ይሁን ጥፋቶች የወጣቶች ሚና ላቀ ያለ ነው፡፡ በሀገራችን ውስጥ የውጭ ወራሪዎችን አሳፍሮ ከመመከት ጀምሮ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች ወጣቶች ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ሰባ በመቶ የሚሆነው የአገራችን ወጣቶች በአገራችንም ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ጉልህ ድርሻ እያበረከቱ ይገኛል፡፡ የአገራችንን የወደፊት መጻኢ እድል የሚወሰነው አሁን ባለው ወጣት በሚያደርጉት አስተዋጽኦ ነው፡፡ ይህም ሲባል ወጣቶች አገር ተረካቢ ትውልድ ለመሆን ራሳቸውን ለሃላፊነት ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡ ሃላፊነት የሚረከብ ሰው በእውቀት መመራት ያሻል፡፡ ያለ እውቀት የሚመራ ስራ መድረሳም መነሻውም አይታወቅም፡፡ ችግር እንኳ ቢፈጠር ሊፈታ የሚችለው በእውቀት በተሞላ ጥበብና አመራር ነው፡፡ ለሚሰሩት ሥራም ምክንያታዊ እንዲሆን ያስችላል፡፡ ከድህነት ለመውጣት በምናደርገው ጥረት ችግሮችን በእውቅትና በጥበብ መፍታት አስፈላጊ ነው፡፡

በጥንት ጊዜ ቀደምት ወላጆቻችን ያስመዘገቧቸው አስደናቂ የሥልጣኔ ገናናነትን ለመመለስ የነበራቸውን ጥንካሬ እና የዓለማ ጽናት መላበስ ያስፈልጋል፡፡ የአገር ወዳድነት ስሜት ባልተበረዘ ባህል ራሳቸውን በመጠበቅ የአገራቸውን ልዕለ ሃያልነት ለማስጠበቅ የሰሩት ሥራ ሁሌም በታሪክ የሚወደሱና የሚታወሱ ናቸው፡፡ ወጣቱም ይህንን የአባቶቻንን ፈለግ በመከተል የድሮን ስንቅ በማድረግ አሁን ያለውን ጥንካሬ በመጠቀም ወደ ፊት መጓዝ ያስችላቸዋል፡፡ በመሆኑም ወጣቶች የአገራችንን እድገት ሊያሻሽሉ የሚችሉ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶችን በማበልጸግ ለቀጣይ ትወልዶች ማስተላለፍ መቻል አለበት፡፡ የቀሰሟቸውን እውቀቶችና ልምዶች ለሌሎች በማስተላፍ የጋራ የአገር ግንባታ ሂደት ያላቸው ሚናም ላቀ ያለ ነው፡፡

መንግሥትም ለወጣቶች ትኩረት በመስጠት የወጣቶችን ልማትና የእድገት ፓኬጅ በመንድፍ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን በተለያዩ የሥራ መስኮች ያጠናቀቁ ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በከተማ ግብርና በሌሎች የስራ መስኮች በማደራጀት የራሳቸውን ሕይወት ከመምራት አልፈው ቤተሰባቸውን ማስተዳደርና ለሌሎች ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር የልማት ዓርበኛ የሚሆኑበትን ሁኔታም ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶች ሥራ ፈጣሪ የሚሆኑበትን ሁኔታ በማመቻቸት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፋጠንም እየተሰራ ነው፡፡ መንግሥት በዘርፉ የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮችን በመፍታት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ማረጋገጥ ይጠበቃል፡፡ በሚፈለገው ደረጃ ያሉትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ረገድ ጥሩ ቢኖሩንም በየደረጃው ያለው አመራር በቁርጥነኝነት ይዞ እንዲፈቱ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት በሚፈለገው ደረጃ ባለመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ሆኖም ግን በአገራገችን በተከሰቱ አንዳንድ አለመረጋጋቶች ውስጥ ጥቂት ወጣቶች በተቃራኒ አቅጣጫ በመመራት የጥፋተኞች ኢላማ ማሳኪያ እየሆኑ ይስተዋላል፡፡ ወጣቶች ባልተገባ ጥቅም ተታለው ወደ አውዳሚና አገራችንን ለባሰ ድህትና ጉስቁልና የሚከት ተግባር ውስጥ መሳተፍ የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም ከብጥብጥ ከሁከት የሚገኝ አንዳች ትርፍ እንደማይገኝ አውቀው ራሳቸውን ወደ ሰላም መንገድ መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡

ሀሳብን በሰከነና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መግለጽ አስተዋይነትና አረቆ አሳቢነትም ነው፡፡ አገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው እርብርብ የመሃል ተዋናኝ እንደመሆናቸው መጠን ከሚያስፈልገው እውቀት እና ክህሎት በተጨማሪ ኢትዮጵያዊ ግብረ-ገብትነትና ጨዋት የተሞላበት በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ለኛ ለኢትዮጵያን መቻቻል አማራጭ የሌለውን የአብሮነታችን መሳሪያ ስልቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ የእድገታችንና አብሮ የመኖራችን ዋስትና ሰላም እንደመሆኑ መጠን ወጣቶች የሰላም ዘብ በመሆን አገር የመገንባት ሚናቸውን አሻራ አስቀመጥመው ማለፍ ይገባቸዋል፡፡