የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ወጣቶች ሊግ 4ኛ መደበኛ ጉባኤን አስመልክቶ ለተሳታፊ የሚዲያ አካላት ስለ ጉባኤው አካሄድ እና ተዛማጅ ጉዳዮች መግለጫ ተሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ እና የአዴፓ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር የሆኑት ጓድ ሙቀት ታረቀኝ ናቸው።

በመግለጫቸው ላይ ዛሬ ላይ ሀገራችን የተጎናፀፈችው ስኬታማ የለውጥ መስመር እውን እንዲሆን ከየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል በላይ ወጣቱ ዋጋ መክፈሉን አንስተው ጉባኤውም በቀጣይ ወጣቶች ሀገራዊ ለውጡን በሰላማዊ መንገድ ማስቀጠል የሚችሉበትን ሁኔታ ጠቋሚ እንደሚሆን ገልፀዋል።

ከ500 በላይ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሎ በሚገመተው በዚህ ጉባኤ ላይ ከአማራ ክልል እና ከኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች የተወጣጡ ተሳታፊዎች እንደሚታደሙ ጓድ ሙቀት ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር የተጀመረው ለውጥ እክሎች ሳይገጥሙት የታሰበለትን ግብ እንዲመታ ጉባኤው ለለውጡ ስኬታማነት አመቺ የሆኑ አቅጣጫዎችን ሊያስቀምጥ እንደሚችል እምነታቸውን ገልፀዋል።

አክለውም ወጣቶች ከስሜታዊነት ርቀው በምክንያታዊነት መሞገት የሚችሉበት አቅም እንዲያዳብሩ እና ለጉባኤው ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋፆ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

ጉባኤው ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ 3 ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በዛሬው እለትም የጉባኤው ተሳታፊዎች በጋራ በመሆን በአባይ ወንዝ ተፋሰስ ዙሪያ በሰባትአሚት ወረዳ በወንዙ ላይ አንዣቦ የነበረውን የአንቦጭ አረም በጋራ በመንቀል አጋርነታቸውን አሳይተዋል።