የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ 4ተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ከጥር 19 ቀን ጀምሮ በሀዋሣ ከተማ ሊካሄድ ነው፡፡

በኢሕአዴግ ወጣቶች ሊግ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ጉባኤ ከሁለት ዓመት እስከ ሁለት አመት ተኩል ጊዜ መካሄድ ይኖርበታል፡፡ በዚሁ መሰረት የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ከጥር 19-21 /2011 ዓ.ም 4ተኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በሀዋሣ ከተማ ያካሂዳል፡፡

የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአዘጋጅ ኮሚቴው ቃል አቀባይ ወጣት ጫላ ኦሊቃ የጉባኤውን ዝግጅት አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ጉባዔው ከእናት ድርጅቱ ጉባኤ ማግስትና ሀገሪቱ በሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቀሴ ባለችበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑ ታሪካዊና ልዩ ያደርገዋል፡፡

ጉባኤውን ለማካሄድ የሚያስችል አስፈላጊው ዝግጅት ሁሉ መጠናቀቁን የገለፀው ቃል አቀባዩ ጉባዔው የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች የሊግ ተወካዮችና ተጋባዥ እንግዶች እንዲሁም የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በደማቅ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ይጀመራል ብሏል፡፡

4ኛው መደበኛ ጉባኤ በ3ኛው መደበኛ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን መነሻ በማድረግ አፈጻጸማቸውን ይገመግማል፡፡ በዚህም ጥንካሬዎች የሚጎለብቱበትንና እጥረቶች የሚታረሙበትን አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል፡፡

ሁሉም የብሄራዊ ድርጅቶች ሊጎች ከህዋስ ጀምሮ አባላትን በማሳተፍ የየራሳቸውን ጉባዔ ሲያካሂዱ መቆየታቸውን ያስታወሰው ወጣት ጫላ ኦሊቃ አባል ሊጎቹ አዳዲስ የተማሩ ወጣቶችን በየደረጃዉ ወደ ሊጉ አመራርነት ማምጣታቸውንም ገልጻል፡፡

4ኛው የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ መደበኛ ጉባኤም በአባል ሊጎች ደረጃ የተጀመሩትን እንቅስቃሴዎች በማጠናከርና በማቀናጀት በሊጉ ውስጥ ዴሞክራሲያዊነትን በሚያሰፋና የሊጉን ተቋማዊ አቅም በሚያጠናክር መልኩ እንደሚካሄድ አስታውቋል፡፡
በዚህም ሊጉ ለአባላትና ለመላው የሀገሪቱ ወጣቶች ጥያቄዎች ምቹ የመታገያ መድረክ ሆኖ የሚያገለግል ተቋም እንዲሆን በማስቻል የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት መፍጠር ይጠበቅበታል ብሏል፡፡

ሊጉ ከመቸዉም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ በመውጣት በወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲሁም በስብዕና ግንባታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ውጤታማ ስራ ለመስራት የሚያስችሉትን አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥም አብራርቷል፡፡

የተጀመረዉን ሀገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል የሚካሄደው ይህ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሀዋሳ ከተማና የአካባቢዋ ነዋሪዎች ሚና የጎላ በመሆኑ በተለመደው የእንግዳ አቀባበል ባህላቸው ለጉባዔው ድምቀት እንዲሰጡት ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

ድልና ድምቀት ለኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ 4ተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ፡፡