ከሁሉ በማስቀደም እንኳን ለሊጋችን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን ለማለት እፈልጋለሁ፡፡

4ኛው መደበኛ ጉባኤያችን በአንድ በኩል በሃገራችን ወጣቶች የለውጥ ፍላጎት በተቀሰቀሰው አመጽ እና በተከፈለው የህይወት ፣ የአካ መጉደል፣የንብረት ፣ የጊዜና የእውቀት መሰዋዕትነት ፍሬ ባፈራበትና በሃገራችን የለውጥ ተስፋ እና ነጻነት መታየት በጀመረበት፣ የሃገራችን ወጣቶች ከመቸውም ጊዜ በላይ ተደራጅቶ የመንቀሳቀስ ፍላጎት ባሳዩበት እና መታየት የጀመረው ለውጥ በወጣቶቻችን ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት ባገኘበትና ለውጡን ለማስቀጠል ግንባር ቀደም ተዋናኝ ለመሆን በተዘጋጀንበት ወቅት የሚካሄድ ጉባኤ በመሆኑ፤ በሌላ በኩል እናት ድርጅታችን ኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በስኬት ባጠናቀቀበትና የሃገራችን ወጣቶች ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ባስተላለፈበት እና በጉባኤው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች መሰረት በማድረግ የሃገራችን ሃብት በግፍ የዘረፉ ሌቦችን ከተደበቁበት ጎሬ እያነቀ ለህግ ማቅረብ በጀመረበትና የህዝባችን በተለይም የወጣቶቻችን ተስፋ በእጅጉ የሚያለመልሙ እርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት ወቅት የሚካሄድ ጉባኤ በመሆኑ ልዩ እና ታሪካዊ ጉባኤ ያደርገዋል፡፡

የተከበራችሁ የሊጋችን አባላት ደጋፊዎችና መላው የሃገራችን ወጣቶች ፡- ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የሃገራችን ህዝብ ለውጥ በሚያፋጥኑ፣ የወጣቶቻችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚያመጡ፣ የሊጋችን አባላት ለትግል በሚያነሳሱ፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በሚያስገነዝቡና መላውን የሃገራችን ወጣቶች በጋራ አጀንዳዎቹ ዙሪያ በሚያነቃንቁ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ የቆየ የፖለቲካ አደረጃጀት ነው፡፡

ሊጋችን ባለፉት አመታት ባደረጋቸው ጥረቶች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በገጠር በግብርና ልማት ስራዎች በከተማ ደግሞ በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ስራዎች እንዲሳተፉና ለህብረተሰባዊ ለውጡ የድርሻቸውን እስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በማድረግ ውጤት ያስመዘገበ አደረጅጀት ነው፡፡ ልማታዊ ዴሞክራሲ መስመር ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ አላማ አንግቦ ከመንቀሳቀስ በተጨማሪ ለእናት ድርጅታችን ኢህአዴግ የአመራር መፈልፈያ ቋት ሆኖ በማገልገል ቀላል የማይባል ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን በሃገራችን ምክንያታዊ የሆኑና ስብዕናቸው የተገነባ ወጣቶች እንዲፈጠሩ ለማድረግ ስልጠናዎችንና የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት መልካም የሚባሉ ጅምሮችን ማሳየት የቻለ አደረጃጀት ነው፡፡

 ከእሳት ባህሪ ጋር ተመሳሳይነት ያለውን የወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ ያለን የህብረተሰብ ክፍል በብቃት መርቶ ለውጤት ማብቃት ከባድ ጥረት ማድረግንና መሰዋዕትን ይጠይቃል፡፡

እሳትን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ምግብን አብስሎ ለጤና ተስማሚ ያደርጋል፣ ብረትን አቅልጦ አስፈላጊ የልማት መሳሪያዎች እንዲመረቱ ያግዛል፣ ሞተርን እንዲንቀሳቀስ በማድረግ የሰው ልጆች ኑሮ ቀለል እንዲል ያደርጋል፡፡

 እሳትን በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ደግሞ የሰው ልጆችን ህይዎት አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ያጠፋል፣ ንብረትን ያወድማል፣ ሃገርን እንዳልነበረች ያደርጋል፡፡

የወጣትነት እድሜን በአግባቡ ከተጠቀምንበት እውቀትም ሆነ ጉልበት ከሱ ጋር ነውና የሰው ልጆች ህይዎት የተሸለ እንዲሆን አስተማማኝ መሰረት ይጥላል፣ የጥሪት ማፍሪያ ጊዜ ሆኖ ያገለግላል፣ ለሃገር ግንባታ የማይተካ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፣ የሃገር ሰላም እንዲረጋገጥ ያደርጋል፡፡

የወጣትነት እድሜ በአግባቡ ካልተያዘና ካልተገራ ደግሞ ተስፋ ቆራጭ ትውልድ ይፈጠራል ፣ የሃገር ሰላም ጠንቅ ይሆናል፣ ለሰው ልጆች ህይዎት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት ይሆናል፣ ለሃገር ትልቅ እድልና ተስፋ መሆን ሲገባው የሃገር ሸክም ይሆናል፣ ልክ እንደ እሳት ሁሉ ለሃገር እንዳልነበረች መሆን ምክንያት ይሆናል፡፡ እሳትን በአግባቡ ተጠቅመን ለመልካም ነገር እንደምናውለው ሁሉ የወጣቶቻችን አመለካከት በመቃኘት፣ አደራጅቶ በማንቀሳቀስ፣ የሚያነሷችው ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲመለሱ በመታገል እና በሃገር ግንባታ ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ መስራት ከመቸውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ በሆነበት ወቅት እንገኛለን፡፡    

ስለሆነም ሊጋችን ባለፉት አመታት ባደረጋቸው ጥረቶች የተመዘገቡ ውጤቶች እንደተተበቁ ሆኖ የተቋቋመለትን አላማ እና አንግቦት የተነሳውን ተልዕኮ ሊያሳካ በሚችል መልኩ እንቅስቃሴ በማድረግ በኩል ያለበት ውስንነት ሰፊ መሆኑን በመገንዘብ የበደለውን ሊያካክስ በሚያስችል ሁኔታ ትግል ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡ በ4ኛው ጉባኤያችን ያለፉትን ሦስት አመታት የተግባር አፈጻጸማችን በውል በመገምገም የሃገራችን ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች /ውሳኔዎች/ የሚቀመጡ ሲሆን ለቀጣይ ሁለት አመታት ሊጋችን በብቃት ሊመሩ የሚችሉ ወጣት አመራሮችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በማስመረጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡

መላው የሃገራችን ወጣቶች ፣የሊጋችን አባላት እና ደጋፊዎቻችንም ለግባችን መሳካት የሚኖራችሁ አስተዋጽኦ በማንም የማይተካ በመሆኑ ዙሪያ ያለኝ መተማመን ትልቅ ነውና ከጎናችን በመሆን ትግሉን እንድታጧጡፉ በዘህ አጋጣሚ ጥሪየን አስተላልፋለሁ፡፡

ድልና ድምቀት ለኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ 4ኛ መደበኛ ጉባኤ

ክብርና ሞገስ ለለውጡ ራሳቸውን ለሰጡ ሰማዕታት

አመሰግናለሁ!!!