የተከበራችሁ የሊጋችን አመራሮችና መላው አባላት ከሁሉ አስቀድሜ የከበረ ሰላምታዬን እያቀረብኩ እንኳን ለ4ኛው መደበኛ ጉባኤአችን በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት ሊጋችን የተለያዩ የሰብዕና ግንባታና በወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ተግባራት ላይ ሲረባረብ ቆይቷል፡፡

በዚህም ለወጣቶች የተለያዩ ዓለምና ሀገር አቀፍ የፅንስ ሀሳብ ውይይቶችና የክርክር መድረኮች በማዘጋጀት የሀገራችን ወጣት ወደ ምክንያታዊ ረድፍ እንዲሰለፍ የጅምር ተግባራት ፈፅሟል፡፡

ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ እንዲሁም በተለያዩ የስራ አማራጮች ወደ ስራ እንዲገቡ በተደረገው ርብርብ በየዓመቱ በየክልሉ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ 

የበጎ ፈቃደኝነት እንዲጎለብት፣ መቻቻልና መፈቃቀር፣ አንድነትና ብዙሃነት የተከበረበት ነባራዊ ሁኔታ ለመገንባት ሊጉ ከፍተኛ የሆነ ርብርብ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በአጠቃላይ ሊጉ ከነጉድለቱም ቢሆን የወከለው የወጣቱ ህብረተሰብ ተገቢ ጥያቄዎች እንዲመለሱና እንዲደመጡ ጠበቃና ልሳን ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡

ይሁንና በአንድ በኩል በሊጉ ተቋም የብቃትና የቁርጠኝነት ችግር በሌላ በኩል ደግሞ በመሪው ድርጅታችንና በመንግስታችን ውስጥ እየጎለበተ የመጣው ፀረ- ዴሞክራሲያዊነት፣ የህዝብንና የወጣቱን ጥያቄዎች በተገቢ አድምጦ ምላሽ የመስጠት ስብዕና መሸርሸር፣ ሌብነትና ዝርፊያ አቅማቸው እየፈረጠመ በመምጣቱና የእኩይ ተግባርና ቡድኖች የበላይነት እየያዘ በመምጣቱ ወደ ስራ ገብቶ ህይወቱ እንዲቀየርለት የሚሻው ወጣት በአመለካከቱና በፅንስ ሀሳብ ዕውቀቱ ብቃት የተላበሰና ምክንያታዊ ሆኖ መቀረፅ የሚገባው ወጣቱ ይህ ጥቅሙ በተገቢ ሳይከበርለት ቀርቷል፡፡  እናም ያለፈው ሶስት ዓመታት ጊዜ በስርዓታችን ውስጥ ገዥ ቦታ እየያዘ የመጣውን ብልሹ ሁኔታዎች ለማስወገድ ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ወቅትም ተፈጥሮ ነበር፡፡

በመሆኑም ይህን እኩይ ሁኔታ ለማስወገድና ሀገራዊ ለውጡን እውን ለማድረግ በድርጅታችንና በህዝብም ውስጥ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበትና ለአዲስ ለውጥ ማለትም ለመብትና ለዴሞክራሲ መስፈን፣ ለፍትሃዊነት መረጋገጥ ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ዕልህ አስጨራሽ ትግልም ተደርጓል፡፡

የእኛ ማህበራዊ መሠረት የሆነውም ወጣት ከለውጥ ፍላጎት ጎን በመሰለፍ በየቀኑ ክቡር ደሙን የገበረበት በሀገራችን ታሪክ ሊረሳ በማይችል መንገድ ለጋ ወጣት ከአፈሙዝ ጋር የተጋፈጠበት ወቅትም ነበር፡፡  የማታ ማታ ግን የለውጥ ሀይሉና ወጣቱ ደሙን ያፈሰሰበት ዓላማ አሸናፊ በመሆን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያቆጠቆጠበት የተንገበገብንለትን የኢትዮጵያዊነት ጥማት በሚደንቅ ሁኔታ መርካት የጀመርንበት የአዲሱ አድማስ በር መከፈት ጀምሯል፡፡

እናም ያለፉት ሶስት ዓመታት በሀገራችንና በድርጅታችን ውስጥ ከፍተኛ ትግል የተደረገበትና በመጨረሻም በለውጡ ሀይል ድል አድራጊነት የተጠናቀቀበት ወቅት ነበር፡፡

በዚህ ሂደት ወጣቶች ከፍተኛ መስዋትነት ከፍለዋል፡፡  እናም ዛሬ በሀገራችን አዲስ የዴሞክራሲህ ጎህ ቀዷል፡፡  የሀሳብ የበላይነት እርግማን አለመሆኑ ተግባራዊ እውቅና ተችሮታል፣ በፍትህዊነት ሰርቶ ለመቀየር፣ ነግዶ ለመክበር ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚያስተናግድ የመንግስት ቢሮክራሲ እየተተከለ ይገኛል፡፡  ለዘመናት ተቆራርጠን የተለየናቸው ኤርትራዊያን ወንድሞቻችን ጋር አዲስ የወንድምነት ህይወት ምዕራፍ ጀምረናል፡፡

የሰፊውን ህዝብ ሀብት ለግል ጥቅማቸው የመዘበሩና አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈፅሙ የቆዩ አካላትንም ለህግ የማቅረብና ተጠያቂ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በአጠቃላይ ወጣቶች መስዋትነት የከፈልንበት ለውጥ በሀገራችን መተግበር ጀምሯል፡፡  በዚህም ሂደት መላው የሀገራችን ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ ተስፋ መታየት ጀምሯል፡፡

በመሆኑም ይህንን ጉባኤ የምናደርግበት ወቅት ለወጣቱ ህይወት መቀየርና ተጠቃሚነት መሠረታዊ የሆኑ እንቅፋቶች በለውጡ ሀይልና በተከፈለው መስዋዕትነት ገለል በተደረገበት ወቅት በመሆኑ ወጣቶችና የአደረጃጀቶቹ መሪዎች ከምንም ጊዜ በላይ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠልና የለውጡን ትሩፋቶች በመጠቀም የወጣቶችን ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ የምንረባረብበት ወቅት ሊሆን ይገባል፡፡

ጉባኤአችንም አሁን ያየነው የነፃነት፣ የፍትሃዊነትና የኢትዮጵያዊ መዋደድና መከባበር ፀሐይ እንዳትጠልቅ የማያደርጉ አቅጣጫዎች የሚመከርበትና ለዚህም ስኬት የሚጠበቅብንን ሁሉ ማበርከት የምንችልበት ልዩ ልዩ ውሳኔዎች የሚወስንበት ሊሆን እንደሚገባ እያሳሰብኩኝ ጉባኤአችን የደመቀና የተሳካ እንዲሆን ልባዊ ምኞቴን እገልፃለሁ፡፡

 

አመሰግናለሁ!!