በቅድሚያ እንኳን ለ4ኛው የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ጉባኤ አደረሰን፤ አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡ ጉባኤያችን የሚካሄድበት ምዕራፍ አገራችን በሁለት ተቋራኒ መፃኢ የእድልና የጥፋት ቋፍ ላይ የምትገኝበት ነው፡፡ ቡሩህ ተስፋ ያዘለው እድላችን ድርጅታችን በለውጥ አራማጆች አመራር ሰጪነት ወደ ጥፋት ሲመሩን የነበሩትን ነጭ ለባሽ ወንጀለኞች አከርካሪ እየሰበሩ ሃገራችን ከገባችበት አጣብቂኝ ለማውጣት እልህ አስጨራሽ ትግል እያደረጉ ያለበት መሆኑ ሲሆን የጥፋቱ ቋፍ ደግሞ ባለፉት ጊዜያት ሲዘራ የቆየው የጥላቻና የፀረ-አንድነት ሴራ እዚህም እዛም በዜጎቻችን መካከል የሚታየው ግጭቶችና ጉዳቶች እንዲሁም የጥፋት ሃይሉ እስከመጨረሻ እስትንፋሱ እራሱን ለማዳን የሚያደርገው አገርን የማሸበር ድርጊት ነው፡፡

አሁን ሀገራችን ያላትን መልካም እድል እያሳደጉ፤ የጥፋት ድግሱን ደግሞ በአንድነት ለመቆምና በፍቅር ለመደመር ወደ ተጨማሪ እድልነት እየቀየሩ ወደ ብልፅግና ከፍታ የሚያደርሱኣትን የቁርጥ ቀን ልጆቿን የምትፈልግበት የትግል ምዕራፍ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል ምዕራፍ ደግሞ አሁን እየተመዘገ ላለው ለውጥ ውድ የሆነ ህይወታቸውን ጭምር ሳይሳሱ ከሰጡ የሀገራችን ወጣቶች በፊት ቀድሞ የሚገኝ አይኖርም፡፡ በመሆኑም ሊጋችን ጉባኤውን ሲያካሂድ ሀገራችንን ከስጋት የሚያላቅቁ የቁርጥ ቀን ወጣቶችን በአገር ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የመሪነት ሚናቸውን እንዲጫወቱ እንዲያስችለን ከባለፉት ጊዜያት ትምህርት ለመውሰድ የሚቻልበት የጠለቀ ግምገማ የምናደርግበት፣ በመላው የሊጋችን መዋቅር የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በዴሞክራሲያዊ ትግል የምንፈጥርበት እና እስከ ቀጣይ ጉባኤያችን አገራችን የተረጋጋች እንድትሆን፣ ወጣቶቻችንም ጥያቄዎቻቸው በዴሞክራሲያዊ መንገድ እየቀረቡ መልስ እንዲያገኙ እና የሊጋችን ተቋማዊ አቅም ተጠናክሮ እንዲወጣ የሚያስችሉ አመራሮች የምንመርጥበትና ግልፅ የሚያሰራ አቅጣጫ የምናስቀምጥበት እንዲሆን መልክቴን እያስተላለፍኩ ጉባኤያችን በስኬትና በድምቀት እንዲጠናቀቅ መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ፡፡