ብርቅዬው ግድባችንን ከዳር ማድረስ-አማራጭ የሌለው ጉዳይ…!

በክሩቤል መርኃጻድቅ
ከስምንት ዓመታት በፊት መላ ኢትዮጵያውንን ቀልብ የሳበ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ተጀመረ፡፡
የአባይ ወንዝ ጥቅም ላይ አለመዋል በቁጭት ሲንገበገቡ የነበሩ መላው ኢትዮጵያውን ደስታቸው ወደር አጣ፡፡ ፕሮጀክቱ
ኃይል ከማመንጨት የዘለለ ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ መላው የሀገራችን ህዝቦች ፕሮጀክቱን ከዳር ለማድረስ
ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኝነታቸውን አሳዩ፡፡ ከህጻን እስከ አዋቂ፣ ተማሪው አስተማሪው፣ መንግስት ሰራተኛው
አርሶ አደሩ …ወዘተ ይህንን ብርቅዬ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ያልተቆጠበ ድጋፋቸውን ሰጡ፡፡
የታላቁ የህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከሌሎች ፕሮጀክቶች ለየት የሚያደርጉት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ የአባይ
ወንዝ ለም መሬታችንንና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን ጠራርጎ እየወሰደ ለሌሎች ሲሳይ፤ ለባለቤቶቹ ደግሞ ጠብ የሚል
ጥቅም ሳይሰጥ መቆየቱ ነው፡፡ የአባይ ወንዝ ለዘመናት የኪነጥበብ ጥበብ ማድመቅያ ሆነ መቆየቱ ህዝቡ የአባይ
ወንዝን ያለ ጥቅም መባከን በየዕለቱ እንዲያስታውስ አድርጎት ቆይቷል፡፡ እናም ፕሮጀክቱ መጋቢት 24ቀን 2003 ዓም
ሲጀመር ከጫፍ እስከ ጫፍ ሁሉንም አነቃነቀ፡፡
ግድቡ ከ6ሺ250 ሜጋ ዋት በላይ በማመንጨት የሀገራችንን የኃይል ዕጥረት በመፍታት ረገድ የሚጫወተው ሚናም
ከፍ ያለ ነው፡፡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የኤሌክትሪክ ኃይል የማይተካ ሚና
አንዳለው እሙን ነው፡፡ እንደ እኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ከላን የውሃ ሃብት ኃይልን ማመንጨት ተመራጭና
ውጤታማም ነው፡፡ ከዚህ በፊት በተከዜ፣ ጊቤና እና ሌሎች ወንዞች ላይ የተሰሩ ግድቦችን ፋይዳ ማየት በቂ ነው፡፡
በሌላ በኩል የግድቡ ግንባታ ሂደት ለሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶች አቅምና ልምድ የሚሰጥ መሆኑ ግድቡ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ
ያለው መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ ግድቡ በአባይ ወንዝ ሊገነባ የሚችልና በርከት ያለ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ የሀገራችን
ይህንን ፕሮጀክት ማሳካት ሌሎች መሰል ፕሮክቶችም በራስ አቅም ለማከናወን ከፍ ያለ የራስ መተማመን የሚፈጥር
ነው፡፡ በተጨማሪም ከሚመነጨው ኃይል በሽያጭ መልክ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ ያስችላል፡፡
ግድቡ ሲጀመር በ5 ዓመታት እንደሚጠናቀቅ ቢገለጽም እስካሁን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡ ይህ መዘግየት
ደግሞ በህዝቡ ዘንድ መሰላቸትን ፈጥሯል፡፡ ግድቡ የተጀመረበት 10ኛው ዓመት ሰሞኑን እየተከበረ ሲሆን በዋናነት
ህዝቡ በግድቡ ላይ ያለውን አመኔታ ለመመለስ እየተሰራ ነው፡፡ የፕሮጅክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሰሞኑን
ለመገናኛ ብዙኃን እንተናገሩት የህዝቡ አመኔታ የታጣበት አንዱ ምክንያት ፕሮጀክቱ ይደርሳል በተባለበት ጊዜ አለመድረሱ
ሲሆን፤ ይሄን በተመለከተም ሆነ በግድቡ ዙሪያ የነበሩ ችግሮችን አስመልክቶ ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ አለመድረሱ
ለህዝቡ አመኔታ መሸርሸር እንደምክንያት ይጠቀሳሉ። ምክንያቱም ግድቡ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የቆየ ቢሆንም ይሄ
መረጃ ተደብቆ፤ ያልተሠራውን እንደተሠራ፤ ሊደርስ ያልቻለውን እንደደረሰ፤ ተደርጎ ለህዝብ ሲገለጽ ነበር ይላሉ፡፡
ኃላፊው ጨምረው በቀጣይ የህዝቡን አመኔታ ለመመለስ ለህዝቡ ትክክለኛ መረጃ ከማድረስ ጀምሮ የሚሠራ ሲሆን፤
ሥራውም ተሠርቶ ህዝቡ በዓይኑ እንዲያይ በማድረግ አመኔታውን ለመመለስ በትኩረት የሚሠራ ይሆናል ብለዋል።
በሂደት ላይ ባጋጠሙ ችግሮች የግድቡን ግንባታ ረዘም ያለ ጊዜ ከመውሰዱ ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮች ውጭ በአራቱም
አቅጣጫዎች ያሉ ኢትዮጵያውን ግድቡን ተጠናቆ ለማየት ያላቸው ጉጉት በቃላት መግለጽ አይቻልም፡፡ መንግስት ከግድቡ
ግንባታ ጋር ተያይዞ አጋጥሞ የነበረውን የመዘግየት ችግር ለመፍታት በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ የኢህአዴግ
ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአንድ ወቅት እንደገለጹት የህዳሴው ግድብ ኢህአዴግ
ከሚፈትነባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ግድቡን ማጠናቀቅ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

አሁን በህዳሴው ግድባችን ዙርያ ሁለት ምርጫ የለንም፤ ያለን ምርጫ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ መላው የሀገራችን
ህዝቦች በትልቅ ተስፋና ጉጉት የሚጠብቁትን ፕሮጀክት በተባበረ ክንድ በማጠናቀቅ ይህ ትውልድ የራሱን ቋሚ ሀውልት
ማኖር፡፡