ዜና ዜና

‹‹በብዙ ጨለማና አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያ ነጻ ማውጣት የሚችለው እውቀት ብቻ ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለትምህርት ወደ ቻይና ለሚሄዱ ተማሪዎች ‹‹በብዙ ጨለማና አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያ ነጻ ማውጣትና ጨለማውን ሊያበራው የሚችለው እውቀት ብቻ ነው›› ሲሉ መልዕክት አስተላለፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ማምሻውን በብሔራዊ ቤተመንግሥት ወደ ቻይና ለሚሄዱ ተማሪዎች በተዘጋጀው የሽኝት መርሐ ግብር ላይ እንደተናገሩት፣ በብዙ ጨለማና አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ያለችዋን አፍሪካንና ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት ጨለማውንም ለማብራት መሠረታዊ ነገር እውቀት ነው ፤ የትምህርት ዕድሉን አግኝተው ወደ ቻይና የሚሄዱ ተማሪዎችም ይህንን በመገንዘብ ራሳቸውን ከውሸካና ከአሉባልታዎች በማራቅ ከትምህርት መልስ ለአገሪቷ ብርሃን ሆነው ማገልገል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው ማሰብ፣ ማሰላሰል፣ መፈላሰፍና ነገን ማየት የሚችሉ ሰዎች ሲፈጠሩ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነጻ የትምህር እድሉን አግኝተው ወደ ቻይና የሚሄዱትም ወደ አገራቸው ሲመለሱ ብርሃን እንዲሆኑ በትልቅ ተስፋ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ሲሄዱ አሁን ላይ ‹‹አገሪቷ ትፈርሳለች›› ተብሎ የሚወራው አሉባልታ ሊያሳስባቸው እንደማይገባና ይልቁንም ኢትዮጵያ በአሥር ዓመት ውስጥ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው አምስት የአፍሪካ አገር ውስጥ እንዷ እንደምትሆን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፍሪካ ውስጥ ያለው ርዕዮተ ዓለም በ19ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ ልሂቃን የፈለሰፉት መሆኑን፤ የ19ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የ21ኛውን ክፍለ ዘመንን ችግር መፍታት እንደማይችልና ችግሩ የሚፈታው ተምሮ ብርሃን በሆነው አዲስ ትውልድ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

በመሆኑም በተለይ ለትምህርት ቻይና የሚሄዱት ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርት ውጭ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ቻይናውያን ወደ ኋላ መቅረት ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ አውቀው የደረሱበትን የአስተሳሰብና የቴክኖሎጂ ምጥቀት ተሞክሮ እንዲወስዱም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ትምህርትን ለማስፋትና የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የተለየ ጥረት የሚያደርግበት ጊዜ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ውጭ ሄደው እንዲማሩ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንና የዚህ ጥረት አካል በሆነው የቻይና የትምህርት ዕድል ዘንድሮ ለአጫጭር ሥልጠና 800 ሰዎች፣ ለሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ከ400 ሰው በላይ ወደ ቻይና እየሄዱ መሆኑን መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከዓለም ከ90 በላይ አገራት በዚህ ዕድል የሚጠቀሙ ሲሆን ኢትዮጵያ 228 ሰዎችን በመላክ ቀዳሚ ተጠቃሚ አገር መሆኗን ጠቅሰዋል።

በሽኝት መርሐ ግብሩ የተገኙት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን በበኩላቸው፤ በየትኛውም አገር ያሉትን ቁልፍ ችግሮች ለመፍታት የተማረ የሰው ኃይል አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ፤ ቻይና በየዓመቱ ለአፍሪካ ከምትሰጠው የትምህርት ዕድል ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተጠቃሚ እንደሆነችና ይህም የሁለቱን አገራት ግንኙነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል። የነጻ የትምህርት ዕድሉ ቀጣይነት እንዳለውና በተለይም ኢትዮጵያ በተማረ የሰው ሀብት እንድትበለጽግ የቻይና አጋርነት እንደማይለያት ተናግረዋል።