ዜና ዜና

ሀገራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ለበለጠ ድል እንዘጋጅ

በአቢ ንጉስ

 

ኢትዮጵያ ከሶስት ሺኅ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያላት ጥንታዊ ሀገር ናት፡፡ ሉአላዊነቷን ሳታስደፍር የቆየች የስልጣኔ መሰረት የሆነች ድንቅ ሀገርም ናት፡፡ እየተፈራረቁ የመጡት የውጭ ወራሪዎች የማሳፈር ታሪክዋ በዋናነት ዜጎቿ በብሄር፣ በሃይማኖት ሳይከፋፈሉ በሀገር ፍቅር ለመስዋዕትነት ዝግጁ መሆናቸው ነው፡፡

 አንድነትና መተባበር ካለ የማይቻል ነገር የለምና ሁሉም የውጭ ወራሪዎች በመቅድላ፣ በመተማ፣ በጉንደት፣ በጉራዕ፣ በዶግዓሊ፣ በአድዋ፣ በካራማራ ወዘተ ሀፍረትን ተከናንበው ተመልሰዋል፡፡ በተለይም የአድዋ ድል ለብዙ ጥቁር አፍሪካዊያን ከቀኝ ገዥዎች እንዲላቀቁ ትልቅ ወኔ እና የድል ተምሳሌት መሆን የቻለ አስደናቂ በዓል ነው፡፡

 ሀገራችን ለብዙ ዘመናት በርካታ የፖለቲካ ክስተቶች እያሰተናገደች መጥቷለች፡፡ እነዚህ ክስተቶች አለመረጋጋት  እየፈጠሩ፤ እነዚህ ክስተቶች ጥፋቶችን እያስከተሉ ለብዙ ዘመናት በድህነት አዙሪት ውስጥ ስትማቅቅ ኖሯለች፡፡ የሀገራችን ህዝቦች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ እኩል ተሳታፊ የሚሆኑበት ስርዓት ለመመስረትም  የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ባካሄዱት መራር ትግል ፍሬ አፍርርቶ  በፌዴራላዊ ስርዓት የምትመራ ሀገር መስርትዋል፡፡

እንሆ ሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት መከተል ከጀመረች ጀምሮ ሃያ ሰምንት አመታት ተቆጠረዋል፡፡ በዚህ የፌዴራላዊ ስርዓት ሂደት በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡ ሲሆን በቀጣይ መፍትሄ የሚሹ ዕጥረቶችም አሉ፡፡

ባሳለፍናቸው ሶስት አመታት እዚህም እዚያም የሚፈጠሩ ችግሮች እየተባባሱ በመምጣቸው ምክንያት የሰላም፣ የአንድነት እና መከባበር መንፈስ እየደበዘዘ አንድነታችን የሚፈታተኑ ችግሮች ተፈጥርዋል፡፡

ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች ለመፍታት በአዲስ ዓመት በአንድነት መነሳት ይኖርብናል፡፡ በርካታ ችግሮችን የተሻገርን ህዝቦች አሁንም በአንድነት ከተነሳን አሁን የገጠሙን ፈተናዎች መሻገር አያቅተንም፡፡ ዋናው ጉዳይ ሁሉንም ችግሮች መሻገር የምንችለው በአንድነትና በትብብር ነው የሚለው አስተሳሰብ መያዝ ነው፡፡

ዜጎች በሀገራቸው በተለያዩ አካባቢዎች ያለምንም ስጋት የመንቀስቃስ፣ የመኖር፣ ሀብት የማፍራት መብት በህገ-መንግስቱ ተቀምጧል፡፡ ሆኖም ህገ-መንግስት ያሰቀመጣቸው መርህዎች እየተሸረሸሩ ዜጎች ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ተዘዋውሮ እንዳይሰሩ፣ ሀብት ማፍራት እንዳይችሉ በተደጋጋሚ የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ ይህ ህገ መንግስታዊ መብት ማክበርና ማስከር ግዴታችን ነው፡፡ ኢህአዴግም የህዝቡን ፍላጎት በመረዳት የዚህ ችግር ዋና ተጠያቂ መሆኑን በማመን  በጥልቅ ተሃድሶ ራሱን በመገምገም ሊቀመንበሩን እስከ መቀየር የደረሰ ለውጥም አደረገ፡፡ ድርጅቱ በጀመረው ለውጥም በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡

በአዲሱ አመት ለውስጣዊ አንድነታችን ትኩረት በመስጠት የተጀመረውን ለውጥ ለማጠናከር መስራት ይገባናል፡፡ በመተባበር መንፈስ የተሻለች ሀገር መገንባት ከቻልን ከሌሎች ሀገሮች ጋር ያለንን ግንኙነትም እየጠናከረ ይሄዳል፡፡ በዚህም የዲፕሎማሲው መስክ የበለጠ አትራፊ መሆን እንችላለን፡፡  

ዘላቂ ግብ ካለን ደግሞ ህዝቡን ከትውልድ ወደ ትውልድ የበለጠ ተጠቃሚ በማድረግ ሀገራችን ብሎም አፍሪካ በኢኮኖሚ ፣በማህበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ይቻላል፡፡

ያለ ሰላም ዴሞክራሲ እና ልማት የለም፤  ፍትህን ማስፈንም አይታሰብም፡፡ በመሆኑም በአንድ አንድ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ችግሮች እና አለመረጋጋቶች በተጠና መልኩ ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ መሰጠት ያሰፍልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ድርሻውን መወጣት አለበት፡፡

 

 

Average (0 Votes)


No comments yet. Be the first.