ዜና ዜና

የ2012 ምርጫ “የሀገራዊ ለውጡ በጎ ተጽዕኖ በተግባር የሚፈተሽበት ይሆናል” ሲል የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም አስታወቁ።

የ2012 ምርጫ "የሀገራዊ ለውጡ በጎ ተጽዕኖ በተግባር የሚፈተሽበት ይሆናል" ሲል የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም አስታወቁ።

የ2012 ምርጫ ከቀደሙት ምርጫዎች የተለየ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ፤ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያካሄደውን ስብሰባ አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ ሰጥተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በሀገሪቷ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

የውይይቱ ዋና ዋና አጀንዳዎችም የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ፣ ምርጫ 2012 እንዲሁም የፓርቲውን የአስር ዓመት እቅድ የተመለከቱ ናቸው።

አቶ ብናልፍ እንደተናገሩት፤ በሀገሪቷ የተለያዩ የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ የሚካሄደው የ2012 ምርጫ ከቀደሙት ምርጫዎች የተለየ ገጽታ ሊኖረው እንደሚችል ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገምግሟል።

የ2012 ምርጫ የሀገራዊ ለውጡ በጎ ተጽዕኖ በተግባር የሚፈተሽበት እንደሚሆን በመግለጽ።

በምርጫው ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሃላፊነት ያለባቸው አካላት በለውጡ እንቅስቃሴ ራሳቸውን በተገቢው መንገድ ማደራጀት እንደሚጠበቅባቸው ነው በውይይቱ ወቅት መነሳቱን ያመለከቱት።

ምርጫው የኢትዮጵያን ገጽታ በአዎንታዊ መልኩ ለማስተዋወቅ መጠቀም እንደሚገባ ኮሚቴው አጽንኦት መስጠቱንም አቶ ብናልፍ ጠቁመዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲካሄድ ያለውን ፍላጎት በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱን አስታውሰው፤ የጸጥታና የፍትህ ተቋማት የህግ የበላይነት እንዲከበር ሃላፊነታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ሊወጡ እንደሚገባም አቅጣጫ ተሰጥቷል።

ምርጫው በሀገሪቷ የተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ የአገሪቷን ገጽታ እየቀየረ መሆኑን ማሳያ እንዲሆን "ብልጽግና ፓርቲ በቁርጠኝነት ሃላፊነቱን ይወጣል" ብለዋል።

በአሁን ወቅት በሃይማኖትና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ትኩረት በማድረግ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ህብረተሰቡን ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ የጣለ መሆኑን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በዝርዝር መገምገሙን ጠቅሰዋል።

የህግ የበላይነት ባለማረጋገጡ ምክንያት በየቦታው ከሚከሰቱ ግጭቶች በመነሳት የ2012 ምርጫ ከዕድል ባለፈ ስጋት ያለበት መሆኑንም ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መገምገሙን አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈ በፖለቲካ ፓርቲዎችና ህብረተሰቡ "የዘንድሮ ምርጫ በዚህ ዓመት መካሄድ የለበትም" የሚሉ አስተያየቶችና ስጋቶች እንደሚነሱም ተናግረዋል።

መንግስት ከምንም ጊዜ በላይ ሰላምና ጸጥታውን ለማረጋገጥ ሲል በጥፋት ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበትም አጽንኦት በመስጠት ኮሚቴው ውሳኔ ማሳለፉንም ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ገደብ መካሄዱ "ለአገሪቷ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" የሚል እምነት እንዳለው አቶ ብናልፍ አስረድተዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ምርጫው "በሀሳብ ትግል ላይ ብቻ ያተኮረ መሆን እንዳለበት ያምናል" ያሉት አቶ ብናልፍ፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ምርጫውን ለማካሄድ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

Average (0 Votes)


No comments yet. Be the first.