መግለጫ መግለጫ

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) ራሱን ISIS ብሎ የሚጠራው የሽብር ቡድን በንጹሃን ኢትዮጵያን ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንደሚያወግዘውና የጸረ አክራሪነትና የጸረ አሸባሪነት ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢህአዴግ ም/ቤት ጽ/ቤት በላከው መግለጫ አስታወቀ፡፡

ኢህአዴግ ISIS የተባለው አሸባሪ ቡድን በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመው አሰቃቂና ዘግናኝ የግፍ ግድያ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ በዜጎቻችን ላይ በተፈጸመው ህገ ወጥ ድርጊት ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማው በመግለፅ ለአደጋው ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝቷል።

የሃማኖት ነጻነትና እኩልነት አስተማማኝ ህገ መንግስታዊ  ጥበቃ በተደረገበት ሁኔታ በአገራችን ለዘመናት ጸንቶ የቆየው በሃይማኖቶች መካከል የመቻቻልና የመከባበር እሴት ለማጥፋትና ሃይማኖትን ለእኩይ የፖለቲካ አላማ መጠቀሚያ ለማድረግ በአክራሪዎችና በአሸባሪዎችን ሲካሄዱ የነበሩና በመካሄድ ላይ ያሉ ህገ ወጥና ጸረሰላም እንቅስቃሴዎችን ኢህአዴግ ከመላ የአገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን በፅናት ሲታገለው እንደቆየና አሁንም እየታገለው መሆኑን መግለጫው አመላክቷል።

 ISIS የሽብር ቡድኑ የፈፀመው ዘግናኝ ተግባር በአሸባሪነትና አክራሪነት ላይ የተጀመረው ትግል አጠናክረን ካልቀጠልን በአገራችንንና በዜጎቻችን ላይ የተጋረጠው አደጋ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነው ያለው መግለጫው ኢሕአዴግ የፀረ ሽብርተኝነትና የፀረ አክራሪነት ትግሉን ከመላ አገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን ይበልጥ አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።

የጸረ አክራሪነትና የጸረ አሸባሪነት ትግላችን አንድ ጊዜ ከሃይማኖት እኩልነትና ነጻነት ጋር ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ጋር በማያያዝ የማደናገሪያ ሃሳብ የሚያቀርቡ የውጭና የአገር ውስጥ ጽንፈኛ ሃይሎች ውግንናቸው ህዝባዊ ባለመሆኑ መላ የአገራችን ህዝቦች ከፅጥታ ሃይላችን ጎን በመሆን አክራሪነትና የጸረ ሽብርተኝነት ትግላቸውን አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል ብሏል ኢህአዴግ በመግለጫው፡፡   

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዜጎቻችን በተለይ ደግሞ ወጣቶች በአገራቸው ሰርተው ሕይወታቸውን የሚለውጡበት ሰፊ እድል በመጠቀም እራሳቸውን በመጥቀም የሀገራቸውን እድገት ሊያፋጥኑ እንደሚገባና ህይወታቸውን አደጋ ውስጥ ከሚጥል ህገ ወጥ ስደት እራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል ብሏል ኢሕአዴግ በመግለጫው።

 


መግለጫ መግለጫ