ከሁሉ በማስቀደም እንኳን ለሊጋችን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን ለማለት እፈልጋለሁ፡፡

4ኛው መደበኛ ጉባኤያችን በአንድ በኩል በሃገራችን ወጣቶች የለውጥ ፍላጎት በተቀሰቀሰው አመጽ እና በተከፈለው የህይወት ፣ የአካ መጉደል፣የንብረት ፣ የጊዜና የእውቀት መሰዋዕትነት ፍሬ ባፈራበትና በሃገራችን የለውጥ ተስፋ እና ነጻነት መታየት በጀመረበት፣ የሃገራችን ወጣቶች ከመቸውም ጊዜ በላይ ተደራጅቶ የመንቀሳቀስ ፍላጎት ባሳዩበት እና መታየት የጀመረው ለውጥ በወጣቶቻችን ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት ባገኘበትና ለውጡን ለማስቀጠል ግንባር ቀደም ተዋናኝ ለመሆን በተዘጋጀንበት ወቅት የሚካሄድ ጉባኤ በመሆኑ፤ በሌላ በኩል እናት ድርጅታችን ኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በስኬት ባጠናቀቀበትና የሃገራችን ወጣቶች ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ባስተላለፈበት እና በጉባኤው ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች መሰረት በማድረግ የሃገራችን ሃብት በግፍ የዘረፉ ሌቦችን ከተደበቁበት ጎሬ እያነቀ ለህግ ማቅረብ በጀመረበትና የህዝባችን በተለይም የወጣቶቻችን ተስፋ በእጅጉ የሚያለመልሙ እርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት ወቅት የሚካሄድ ጉባኤ በመሆኑ ልዩ እና ታሪካዊ ጉባኤ ያደርገዋል፡፡

የተከበራችሁ የሊጋችን አባላት ደጋፊዎችና መላው የሃገራችን ወጣቶች ፡- ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የሃገራችን ህዝብ ለውጥ በሚያፋጥኑ፣ የወጣቶቻችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚያመጡ፣ የሊጋችን አባላት ለትግል በሚያነሳሱ፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በሚያስገነዝቡና መላውን የሃገራችን ወጣቶች በጋራ አጀንዳዎቹ ዙሪያ በሚያነቃንቁ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ የቆየ የፖለቲካ አደረጃጀት ነው፡፡

ሊጋችን ባለፉት አመታት ባደረጋቸው ጥረቶች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በገጠር በግብርና ልማት ስራዎች በከተማ ደግሞ በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ስራዎች እንዲሳተፉና ለህብረተሰባዊ ለውጡ የድርሻቸውን እስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በማድረግ ውጤት ያስመዘገበ አደረጅጀት ነው፡፡ ልማታዊ ዴሞክራሲ መስመር ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ አላማ አንግቦ ከመንቀሳቀስ በተጨማሪ ለእናት ድርጅታችን ኢህአዴግ የአመራር መፈልፈያ ቋት ሆኖ በማገልገል ቀላል የማይባል ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን በሃገራችን ምክንያታዊ የሆኑና ስብዕናቸው የተገነባ ወጣቶች እንዲፈጠሩ ለማድረግ ስልጠናዎችንና የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት መልካም የሚባሉ ጅምሮችን ማሳየት የቻለ አደረጃጀት ነው፡፡

 ከእሳት ባህሪ ጋር ተመሳሳይነት ያለውን የወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ ያለን የህብረተሰብ ክፍል በብቃት መርቶ ለውጤት ማብቃት ከባድ ጥረት ማድረግንና መሰዋዕትን ይጠይቃል፡፡

እሳትን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ምግብን አብስሎ ለጤና ተስማሚ ያደርጋል፣ ብረትን አቅልጦ አስፈላጊ የልማት መሳሪያዎች እንዲመረቱ ያግዛል፣ ሞተርን እንዲንቀሳቀስ በማድረግ የሰው ልጆች ኑሮ ቀለል እንዲል ያደርጋል፡፡

 እሳትን በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ደግሞ የሰው ልጆችን ህይዎት አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ያጠፋል፣ ንብረትን ያወድማል፣ ሃገርን እንዳልነበረች ያደርጋል፡፡

የወጣትነት እድሜን በአግባቡ ከተጠቀምንበት እውቀትም ሆነ ጉልበት ከሱ ጋር ነውና የሰው ልጆች ህይዎት የተሸለ እንዲሆን አስተማማኝ መሰረት ይጥላል፣ የጥሪት ማፍሪያ ጊዜ ሆኖ ያገለግላል፣ ለሃገር ግንባታ የማይተካ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፣ የሃገር ሰላም እንዲረጋገጥ ያደርጋል፡፡

የወጣትነት እድሜ በአግባቡ ካልተያዘና ካልተገራ ደግሞ ተስፋ ቆራጭ ትውልድ ይፈጠራል ፣ የሃገር ሰላም ጠንቅ ይሆናል፣ ለሰው ልጆች ህይዎት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት ይሆናል፣ ለሃገር ትልቅ እድልና ተስፋ መሆን ሲገባው የሃገር ሸክም ይሆናል፣ ልክ እንደ እሳት ሁሉ ለሃገር እንዳልነበረች መሆን ምክንያት ይሆናል፡፡ እሳትን በአግባቡ ተጠቅመን ለመልካም ነገር እንደምናውለው ሁሉ የወጣቶቻችን አመለካከት በመቃኘት፣ አደራጅቶ በማንቀሳቀስ፣ የሚያነሷችው ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲመለሱ በመታገል እና በሃገር ግንባታ ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ መስራት ከመቸውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ በሆነበት ወቅት እንገኛለን፡፡    

ስለሆነም ሊጋችን ባለፉት አመታት ባደረጋቸው ጥረቶች የተመዘገቡ ውጤቶች እንደተተበቁ ሆኖ የተቋቋመለትን አላማ እና አንግቦት የተነሳውን ተልዕኮ ሊያሳካ በሚችል መልኩ እንቅስቃሴ በማድረግ በኩል ያለበት ውስንነት ሰፊ መሆኑን በመገንዘብ የበደለውን ሊያካክስ በሚያስችል ሁኔታ ትግል ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡ በ4ኛው ጉባኤያችን ያለፉትን ሦስት አመታት የተግባር አፈጻጸማችን በውል በመገምገም የሃገራችን ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች /ውሳኔዎች/ የሚቀመጡ ሲሆን ለቀጣይ ሁለት አመታት ሊጋችን በብቃት ሊመሩ የሚችሉ ወጣት አመራሮችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በማስመረጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡

መላው የሃገራችን ወጣቶች ፣የሊጋችን አባላት እና ደጋፊዎቻችንም ለግባችን መሳካት የሚኖራችሁ አስተዋጽኦ በማንም የማይተካ በመሆኑ ዙሪያ ያለኝ መተማመን ትልቅ ነውና ከጎናችን በመሆን ትግሉን እንድታጧጡፉ በዘህ አጋጣሚ ጥሪየን አስተላልፋለሁ፡፡

ድልና ድምቀት ለኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ 4ኛ መደበኛ ጉባኤ

ክብርና ሞገስ ለለውጡ ራሳቸውን ለሰጡ ሰማዕታት

አመሰግናለሁ!!!

 

 

 

 

የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸዉ ተግባራት በአጭሩ ምን ይመስላል?

የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሀገራችን የወጣቶች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን በማሳደግ በሀገር ግንባታ ሂደት እና በፖለቲካ  የወጣቶችን ሚና ለማሳደግ የማይናቅ ተግባራትን ሲያከናዉን ቆይተዋል፡፡  ባለፉት ሶስት ዓመታትም የህንኑ አጠናክሮ የቀጠለ ስሆን የወጣቶችን አመለካከት ለመገባትም የተለያዩ የስልጠና እና የዉይይት መድረኮችን በመክፈት የስብዕና ግንባታ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡

በተለይ በቅርብ ጊዜ ሊጉ ከተለመደው አሰራር ወጣ ባለመልኩ የስብዕና ግንባታ ዘዴዎችን ቀይሶ ተንቀሳቅሷል፡፡ ለአብነት የወጣቶች ምክንያታዊ የውይይትና የክርክር መድረክ፣ የተለያዩ ዝግጅቶችን ማዕከል በማድረግ የስብዕና ግንባታ ሥራዎችን ለመስራት ተንቀሳቅሳል፡፡ ይሁን እነዚህ ተግባራቶች በወጣቱ ዘንድ ያመጣውን ለውጥ እየገመገሙ የመምራት፣  የተከታታይነት እና የአጀንዳ ተደራሽነት ጋር ተያይዞ ያለዉ ችግር ሰፊ ነዉ፡፡ ስለሆነም ይህንን ችግር በሚያርም መንገድ ተግባራቱ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ መከናወን አለበት፡፡

ከወጣቶች ፖለቲካ ተሳትፎና ተጠቃሚነት አንፃር የሊግ መዋቅራችን እንዲጠናከርና የመድረኩን ተልዕኮ ተገንዝቦ ለተፈፃሚነቱ እንዲረባረብ ብቻም ሳይሆን የሚወክለዉን የህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲታገል ለማድረግ ለአመራራችንና አባላችን በተወሰነ ደረጃ የዓቅም  ግንባታ  ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በዚህም ሊጉ በድርጅት ግንባታ የእናት ድርጅት ክንፍ በመሆን ወጣቶች በአመራርነት በተለይም በጀማሪ እና መካከለኛ አመራር ደረጃ  ተሳታፊ በመሆን ለተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ አጋዥ በመሆን የበኩላቸውን አሰተዋጽኦ እንዲጫወቱ   ማድረጉንና እያደረገ መሆኑን እንዲሁም በሂደቱም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ከወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እያዛመደ ተቋሙን ለተሻለ ደረጃ ለማብቃት እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡

ከወጣቶች ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አንፃር መንግስት የጀመረውን ጠንካራ ድጋፍ እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀምና ከሚመለከታቾ አካላት ጋር በመቀናጀት የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን በማመቻቸት፤ የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግና በዘርፉ የሚታዩ የብልሹ አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ በኩል አበረታች እንቅስቃሴ ተደርገል፡፡

ከማህበራዊ ልማት ሥራችን አንጻር በትምህርት፣ በጤና፣ በወጣቶች መዝናኛ እና በወጣቶች ስብዕና ግንባታ ማዕከላት  እና የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት እንዲጎለብት፣ ርብርብ በማድረግ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

በዚህም  አበረታች ዊጤቶች ቢኖሩም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለበት እና  የሚታዩ ጉድለቶችም ሰፍ በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡

ከሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት አንፃር  በሀገራችን እየታየ ያለውን ለውጥ በእምነት ከመቀበል እና አፍራሽ የሆኑ አጀንዳዎችን በመፈብረክ በህዝቦች መካከል ጥርጣሬንና ግጭት እንዲፈጠር ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ወጣቱን በማህበራዊ ሚዲያ በመቀስቀስ የሚከሰቱ ችግሮችን የወጣቱን ስብዕና ገንብቶ ከመቀልበስና ከመከላከል አንፃር እየተሰራ ያለው ስራ ቢኖርም በብዙ ጉድለቶች የተተበተበ በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት መስራት ይጠይቃል፡፡

ከህዝብ ግንኙነት ስራም አንፃር ትኩረት ሰጥቶ መስራትና  በሊጉ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተከታታይነት መልዕክት የመልቀቅ፤ መልዕክቶችም ሳቢ፣ አዝናኝና ወቅታዊ ከማድረግ አንፃር የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች አበረታች ቢሆንም፤ ጉድለት እንዳለበትና በዚህም ጉድለት  የሊጉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሰፊ ተከታይ ማፍራት እንዳልቻሉና ሳቢ አለመሆኑ ታይተዋል፡፡ ስለሆነም ይህንን ጉድለት በየ ደረጃዉ ያለዉ መዋቅራችን በፍጥነት ማረምና ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡

የሊጉን ተቋማዊ አደረጃጀት እና ቁመና  በሁሉም ደረጃ ከሀገራዊ ለውጡ ጋር የሚራመድ ተቋማዊ አደረጃጀት ከመፍጠርና መሰረቱን በጥራት ከማስፋት አንጻር የተሰራ ስራ ቢኖርም ደካማ በመሆኑ  እስከ ህዋስ የተደራጀው መዋቅራችን ከድክመቱ ተላቆ በፍጥነት ወደ ተግባር በመግባት ውጤታማ ሥራ መስራት አለበት፡፡

ሊጉ ባሳለፋቸዉ ዓመታት የእናት ድርጅት ድጋፍና ክትትል ምን ይመስላል?

እናት ድርጅታችን  የሊጋችን ተቋማዊ አቅም ለመገንባት በአደረጃጀትና አሰራር፣ በሰው ሃይልና ግብዓት ያሉብንን ጉድለቶች በመሙላት፤ በመተዳደሪያ ደንብ የተሰጠውን ተነፃፃሪ ነፃነት እንዲከበር ከማድረግ እና ተገቢዉን ክትትልና ድጋፍ ከማድረግ አንፃር ያለዉ ሁኔታ በየደረጃዉ  የተለያየ ቢሆንም በጅምር ደረጃ አበረታች ነዉ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በየደረጃው በሚገኙ አንዳንድ የእናት ድርጅት አመራሮች ዘንድ ሊጋችን ለሚያከናውናቸው ተግባራት ድጋፍ ከማድረግ፤ ተገቢውን እውቅና በመስጠት እንዲጠናክሩ ከማድረግ፣  ይልቅ ሊግን አሳንሶ የማየትና ያለአግባብ የመፈረጅ የተዛባ አተያይ በዉስን ደረጃ የሚታይ ስለሆነ መስተካከል አለበት ፡፡

በአጠቃላይ ባሳለፍነዉ ዓመታት በሰራናቸዉ ስራዎች መልካም ጅምር ላይ ብንገኝም፤ ከተሸከምነዉ ተልዕኮና ከአገራችን ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር ከፍተኛ ጉድለት ስላለብን  ሰፊ ስራ ይጠይቀናል፡፡

ከሊጉ መደበኛ 4 ጉባኤ የሚጠበቁ ተግባራት ምንድን ናቸዉ ?

የሊጉ መደበኛ ጉባኤ በሊጉ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ከሁለት ዓመት እስከ ሁለት አመት ተኩል ጊዜ መካሄድ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡  በዚሁ መሰረት አሁን ያለንበት ወቅት በብዙ ምክኒያቶች ታሪካዊና ልዩ ሁኔታ ዉስጥ ሁነን በምናካሂደዉ 4ኛ መደበኛ ጉባኤያችን ያስቀመጥናቸዉን አቅጣጫዎች መነሻ በማድረግ አፈጻጸማችንን በብቃት በመገምገም፤ ጥንካሬያችንን በማጎልበትና እጥረታችንን ማረም የሚያስችሉንን ዝርዝር አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡

በሌላ በኩል በሊጉ ውስጥ ዴሞክራሲያዊነትን በሚያሰፋና የሊጉን ተቋማዊ አቅም በሚያጠናክር እና ለአባላትና ለመላው የሀገራችን ወጣቶች ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ምቹ የመታገያ መድረክ ሆኖ የሚያገለግል ተቋም እንዲሆን በሚያስችል መልኩ እና ሁሉንም የሊጉን አባላት በማሳተፍ ከህዋስ ጀምሮ በንቅናቄ ማካሄድ   እና በየደረጃዉ  አዳዲስ የተማሩ ወጣቶች ወደ ሊጉ አመራርነት የሚቀላቀሉበትና የተሻለ አደረጃጀት በመፍጠር በድምቀትና በስኬት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

በቀጣይ ከሊጋችንና ከወጣቱ የሚጠበቁ ተግባራት?

ሊጋችን ከመቸዉም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ የሚወጣ ሲሆን የወጣቶችን ስብና ግንባታ በማሳደግና ከተለያዩ ወጣት አደረጃጀቶች ጋር በወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚኔት ላይ ተቀናጅቶ ዊጤታማ ስራ መስራት፡፡

በተሌይ ስራ አጥ የሆኑ ወጣቶችን ከመለየት ጀምሮ ያሉ የግንዛቤ ፈጠራ፣ በቂ የክህሎትና የሙያ ስልጠና፣ የማደራጀትና በቂ ግብዓት የማቅረብና የገበያ ትስስር የመፍጠር ችግሮች ሰፊ ስለሆኑ ኢንዲታረሙ መስራት ያስፈልጋል፡፡

 

በአገራችን መታየት የጀመረው ተስፋ ሰጭ የለውጥ እንቅስቃሴ በተከፈለዉ የህይወት፣ የአካል፣ የገንዘብ፣ የእውቀትና የጊዜ መስዋትነት የመጣ መሆኑን በመገንዘብ ለውጡን ሊያደናቅፉ የሚችሉ አልፎ አልፎ የሚታዩ ክፍተቶችን ፈጥኖ የማስተካከል ስራ መስራትና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት አስተሳሰብን ማጎልበት፣ መጥፎ አስተዳደርንና ሌብነትን አምርሮ መታገል፤ የሕግ የበላይነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ሕግንና ሕገ-መንግሥቱን መሠረት በማድረግ መቀሳቀስ፤ ለሐሰተኞች፣ ለአሉባልተኞች እና የአገራችንን ሰላም ለማይፈልጉ ኃይሎች መጠቀሚያ ከመሆን በመቆጠብ  ምክንያታዊና የለውጡ ግንባር ቀደም ተዋናዬች በመሆን መቀሳቀስ፡፡ በተሰማሩበት የስራ መስክ ሁሉ ግንባር ቀደም ሚናን በመጫወትና ለሌሎችም ሞዴል በመሆን በሁሉም ዘርፍ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት  ያስፈልጋል፡፡

   

ድልና ድምቀት ለኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ 4 መደበኛ ጉባኤ